በጌዴኦ ዞን የሚገኙ ተፈናቃይ ዜጎችን ለመደገፍ ጥረት እየተደረገ ነው

118

ዲላ መጋቢት 4/2011 በጌዴኦ ዞን ተጠልለው አስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፍ ለሚሹ  ተፈናቃይ ዜጎች ምላሽ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ  ዋና አስተዳደሪ አቶ ገዙ አሰፋ ገለጹ፡፡       

ዋና አስተዳዳሪው በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት መንግስት አካባቢውን ከታጠቁ ኃይሎች ለማጥራት እየወሰደ ያለውን እርምጃ ተከትሎ በመረበሽ የሸሹ ከ37 ሺህ በላይ ዜጎች በዞኑ  ገደብ ወረዳ ጎቲቲ ቀበሌ ተጠልለው ይገኛሉ፡፡

ይህም ባለፈው ዓመት በጌዴኦና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች አካባቢ በነበረው ችግር በመፈናቀል ተጠልለው በመቆየት ወደ አካባቢያቸው ሳይመለሱ የቀሩትን አይጨምርም፡፡

እነዚህ ወገኖች የምግብ እጥረት የገጠማቸው በመሆኑ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ከክልልና ከፌዴራል መንግስት ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የዞኑ አስተዳደር ሀብት በመመደብና ከተለያዩ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ጋር በመተባበር አነዚህን ወገኖች ለመታደግ ጥረት  እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

አቶ ገዙ እንደተናገሩት  ለመጀመሪያ ዙር 30 ሺህ ኪሎ ግራም ዱቄት  ለተፋናቃዮቹ እየቀረበ ነው፤ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ሐዋሳ ቅርንጫፍም  25 ሺህ ኪሎ ግራም አልሚ ምግብ ለማቅረብ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡

ለቀጣይ አንድ ወር የሚሆን ምግብ ለማቅረብ ደግሞ ከአለም ምግብ ድርጅት ጋር ከስምምነት መደረሱን ጠቅሰው ሌሎች ድርጅቶችም ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ወደ አካባቢው ማድረስ መጀመራቸውን አስታውቀዋል፡፡

በአሁን ወቅት በዞኑ ከ172 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች እንደሚኖሩ ያመለከቱት ዋና አስተዳዳሪው ከሰብአዊ ድጋፍ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል ፡፡

" የተፈናቀሉ ዜጎች ወደአካባቢያቸው ተመልሰው በዘላቂነት የሚቋቋሙበት ሁኔታ ለመፍጠር የጌዴኦና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች ጥረት እያደረጉ ነው" ብለዋል፡፡

የጌዴኦ ብሔር ዘመን መለወጫ" ዳራሮ"  በዓልን ምክንያት በማድረግ ከሀገር ውስጥና ከውጭ  ከሚመጡ የዞኑ ተወላጆችና ባለድርሻ አካላት  ጋር በድጋፍ  ዙሪያ ለመምከርም ታቅዷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም