የኢትዮጵያና የግብፅን የረጅም ዘመናት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እሰራለሁ- አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

501

መጋቢት 4/2011 በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል ያለውን የረጅም ዘመናት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚሰሩ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናግረዋል።

በግብጽ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባለሙሉስልጣን አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ትናንት አቅርበዋል።

በግብጽ ቆይታቸው ረጂም ዘመናትን የተሻገረው የሁለቱ ሀገራትግንኙነት የላቀ እመርታ እንዲያሳይ አበክረው እንደሚሰሩ አምባሳደር ዲና በዚሁ ወቅት ለፕሬዝዳንት አል ሲሲ ገልጸውላቸዋል።

ፕሬዚዳንት አልሲሲ በበኩላቸው በኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር 302 አውሮፕላን ላይ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም በደረሰዉ አደጋ ህይወታቸዉን ላጡ ዜጎች የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልጸዋል።

ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያና ግብጽ እጣ የተሳሰረ መሆኑንና ያለው አማራጭም አብሮ የመስራት፣ የመልማትና የማደግ መሆኑን ነው ፕሬዚዳንቱ የገለፁት።

አምባሳደር ዲና በግብጽ በሚኖራቸው ቆይታ የሀገሪቱ ህዝብና መንግስት ድጋፍ እንደማይለያቸው ፕሬዚዳንት አል ሲሲ አረጋግጠውላቸዋል።

አምባሳደር ዲና ተቀማጭነታቸው በግብፅ ሆኖ በሊቢያ፣ በጆርዳን እና በሌባኖስ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው እነደሚያገለግሉ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።