ብሪታኒያ የቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን በረራን ላልተወሰነ ጊዜ አገደች

78

አዲስ አበባ መጋቢት 3/2011 ብሪታኒያ በኢትዮጵያ የተከሰከሰውን ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋ ተከትሎ ተመሳሳይ አውሮፕላኖች ላልተወሰነ ጊዜ በአየር ክልሏ በረራ እንዳያደርጉ አገደች።

ብሪታኒያን ተከትለው በርካታ ቁጥር ያላቸው አገሮች ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን በረራ እንዳያደርግ እገዳ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

ከትላንት በስቲያ ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ሲበር የነበረው ንብረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ቢሾፍቱ አካባቢ መከስከሱ ይታወቃል።

የበረራ ቁጥሩ ኢቲ 302 የሆነው ይህ አውሮፕላን 149 መንገደኞችንና 8 የበረራ ሰራተኞችን አሳፍሮ በረራ ከጀመረ ከስድስት ደቂቃ በኋላ በመከስከሱ በውስጡ የነበሩ 157 ሰዎች ህይወት አልፏል።

የእንግሊዙ የዜና ምንጭ ቢቢሲ የብሪታኒያ የሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣንን ጠቅሶ እንደዘገበው በብሪታኒያ የአየር ክልል ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች በረራ እንዳያደርጉ ላልተወሰነ ጊዜ አገሪቱ ማገዷን አስታውቃለች። 

የብሪታኒያ የሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ከዚህ ውሳኔ የደረሰው አሁን ባለው ሁኔታ ትናንት ከተገኘው የመረጃ ሳጥን ስለ አደጋው በቂ የሚባል መረጃ ባለማግኘቱ እንደሆነ ገልጿል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተዓማኒነትና ተቀባይነት ያለው የብሪታኒያ የሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ከዚህ ውሳኔ ላይ መድረሱ ለአሜሪካው አውሮፕላን አምራች ቦይንግ ትልቅ አደጋ እንደሆነ የዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን በመዘገብ ላይ ይገኛሉ።

በተጨማሪም የብሪታኒያ አቪዬሽን ተቋም ውሳኔ በተቀረው የአውሮፓ አህጉርና አሜሪካ የሚገኙ የሲቪል አቪዬሽን ተቆጣጣሪዎች ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ የሚያስገድድ እንደሆነም በመነገር ላይ ነው።

የባለስልጣኑን ውሳኔ ተከትሎ ፈረንሳይ፣ ጀርመንና አየርላንድ የቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች ላልተወሰነ ጊዜ በረራ እንደያደርግ ማገዳቸውን አስታውቀዋል። 

የብሪታኒያ ግዙፉ የቻርተር አየር መንገድ 'ቱይ ኤርዌይስ'ና የኖርዌው ግዙፍ አየር መንገድ 'ኖርዌጂያን ኤር' የቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች ላልተወሰነ ጊዜ በረራ እንዳያደርጉ አግደዋል።

ህንድ፣ አውስትራሊያ፣ ሲንጋፖር፣ ኦማንና ማሌዢያ  ዛሬ የቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች ላልተወሰነ ጊዜ በረራ እንዳያደርጉ ያገዱ ሌሎች አገሮች ናቸው።

ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ብራዚል፣ ሜክሲኮ፣ ኢንዶኔዢያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ አርጀንቲና፣ ዚምባቡዌ፣ የኬይማን ደሴቶችና ፊጂ አውሮፕላኑ በረራ እንዳያደርግ ውሳኔ ያስተላለፉ አገሮች ናቸው።

አሜሪካ፣ አይስላንድና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከተማ የሆነችው ዱባይ ከአደጋው በኋላ አውሮፕላኑ አሁንም አገልግሎት እየሰጠባቸው ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢትዮጵያ የተከሰከሰውን ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋ ተከትሎ ተመሳሳይ አውሮፕላኖች ላልተወሰነ ጊዜ በረራ እንዳያደርግ ያገዱ አገሮች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል።

ይሄንኑ ተከትሎ በአውሮፕላኑ ሞዴል የደህንነት ጥያቄ በከፍተኛ ሁኔታ እያስነሳ የሚገኝ ቢሆንም የአሜሪካ የአቪዬሽን አስተደዳደር ''አውሮፕላኖቹ አሁንም ለበረራ ብቁ ናቸው ከበረራ የሚታገዱበት ምክንያት የለም የምርመራው ውጤት ሳይታወቅ እርምጃ አልወስድም'' ብሏል።

በኢትዮጵያ ከትላንት በስቲያ ከደረሰው የመከስከስ አደጋ በተጨማሪ ከጥቂት ወራት በፊት ላየን ኤይር የተሰኘ የኢንዶኔዚያ አየር መንገድ ንብረት የሆነ ተመሳሳይ ሞዴል ከመሬት ከተነሳ ከ18 ደቂቃ በኋላ ተከስክሶ የ189 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል።

የበረራ ባለሙያዎች ''በኢትዮጵያው የተከሰተው የአውሮፕላን አደጋ ከሞዴሉ ጋር ስለመያያዙ ለመናገር ጊዜው ገና መሆኑን እየጠቀሱ ሲሆን ነገር ግን ሁለቱም አደጋዎች ቦይንግ 737 ማክስ 8 ላይ መድረሳቸውና አውሮፕላኖቹ በተነሱ በደቂቃዎች ውስጥ አደጋዎቹ መድረሳቸው ያመሳስላቸዋል'' ብለዋል።

የአሜሪካው አውሮፕላን አምራች ቦይንግ ኩባንያ ከትላንት በስቲያው ከአደጋው በኋላ በዓለም ደረጃ ያለው የአክሲዮን ድርሻ በ12 በመቶ መቀነሱም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም