ፍርድ ቤቱ በአዶላ የተያዘው 100 ኩንታል ስኳር እንዲወረስና አሽከርካሪው በገንዘብ እንዲቀጣ ወሰነ

64

ነጌሌ መጋቢት 3/2011 በሕገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ በአዶላ ከተማ የተያዘ 100 ኩንታል ስኳር እንዲወረስና አሽከርካሪው በገንዘብ እንዲቀጣ በጉጂ ዞን የአዶላ ወረዳ ፍርድ ቤት ወሰነ፡፡

ፍርድ ቤቱ ቅጣቱን የወሰነው  ስኳሩ በሕገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ በፖሊስ እጅ ከፍንጅ በመያዙ እንደሆነ የወረዳው ፍትህ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጉተማ ጫልቲሳ ገልጸዋል፡፡

ስኳሩ በኮድ 3 ሠሌዳ ቁጥር 24269 አዲስ አበባ በሆነ ተሽከርካሪ በሕገወጥ መንገድ ከነጌሌ ከተማ ተጭኖ አዶላ ከተማ የካቲት 26/2011 ነበር የተያዘው፡፡

ስኳሩ ሕጋዊ የጉዞ ሰነድና ማስረጃ ባለመያዙ  እንዲወረስና አሽከርካሪው ደግሞ 3 ሺህ ብር ቅጣት እንደተወሰነበት አስረድተዋል፡፡

የአዶላ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ዋና ሳጂን ጉተማ ሳፋዬ ሕዝቡ በመሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ ከሚፈጸም የኢኮኖሚ አሻጥር ለመዳን ሕገወጥ ንግድን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝ ጠይቀዋል፡፡

ያለ ሕጋዊ ፈቃድ በተሳሳተና ሕጋዊ ባልሆነ ሰነድ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ አካባቢ የሚጓጓዝ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ፍትሃዊ የንግድ ውድድርን እንደሚያዛባም አመልክተዋል፡፡

ፖሊስ ሕገወጥ እንቅስቃሴዎ ለመከላከል የጀመረውን ጥረት አጥፊዎችን ሕግ ፊት በማቅረብ እንደሚያጠናክር ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም