የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በላሊበላ ጉብኝት እያደረጉ ነው

64

አዲስ አበባ መጋቢት 3/2011 ለሁለት ቀናት በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት የሚያደርጉት የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በላሊበላ ጉብኝት እያደረጉ ነው።

ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ዘመናትን የተሻገረ የሁለትዮሽ ግንኙነት አላቸው።

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በላሊበላ  አየር መንገድ  ተገኝተው ለፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን  አቀባበል አደርገውላቸዋል።

በአቀባበል ስነ ስርዓት ላይ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር ዶክተር አምባቸው መኮንን፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው፣ የላሊበላ ከተማ ነዋሪዎችና የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።  

ለፕሬዚዳንት ማክሮን ክብር ሲባልም ዘጠኝ ጊዜ መድፍ ተተኩሷል።

የፕሬዚዳንቱ የላሊበላ ጉብኝት ዓላማ ቅርሱ በአሁኑ ወቅት ያለበትን ጉዳትና ቅርሱን ከጥፋት ለመታደግ የፈረንሳይ መንግስት ሊያደርግ የሚገባውን ድጋፍ ለማጤን መሆኑም ተገልጿል። 

ባለፈው ጥቅምት ወር ጠቅላይ ሚንስትር ዶከተር አብይ በፈረንሳይ ባደረጉት ጉብኝት ከፕሬዝዳንት ማክሮን ጋር ውይይት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።

ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ረዥም ዘመን ያስቆጠረው ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ግንኙነት ያላቸው አገሮች ሲሆኑ የግንኙነታቸው መጠናከር የጀመረው ከ17ኛው ክፍለ ዘመን በፊት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በሚጠቀሰው ቄስ ጆን ዘመን መሆኑን የተለያዩ ታሪካዊ መዛግብቶች ያሳያሉ።

የአገሮቹ ግንኙነት እየተጠናከረ ሲመጣ እአአ በ1843 በኢትዮጵያና በፈረንሳይ መካከል የወዳጅነትና የንግድ ስምምነት በወቅቱ የኢትዮጵያ የሸዋው ንጉስ ሳህለስላሴና በፈረንሳዩ ሊዩስ ፊሊፕ ተደረገ።

ግንኙነታቸው ተጠናክሮ ኢትዮጵያ የአድዋ ድልን ከተቀዳጀች በኋላ ፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ጋር በየካቲት ወር እአአ 1897 የኢትዮ-ጂቡቲ የድንበር ስምምነት በመፈራረም ማጠናከር ተችሏል።

በዚሁ ዓመት ተጀምሮ ከ20 ዓመት በኋላ የተጠናቀቀው የኢትዮ-ጂቡቲ መስመር ዝርጋታና ግንባታ በአገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ማጎልበት ቻለ።

እአአ በ1904 የኢትዮጵያና የፈረንሳይ የወዳጅነት ቢሮ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ መከፈቱ ለግንኙነታቸው መጠናከር የበኩሉን ሚና ተጫውቷል።

እአአ በ1907 ፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ የፈረንሳይ ኤምባሲ በኢትዮጵያ ከፍታለች።

ከዚያ በኋላ እአአ በ1943 የኢትዮጵያና የፈረንሳይ የባህል ትብብር ማዕከል፣ በ1947 ሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት፣ በ1955 የፈረንሳይ አርኪኦሎጂ ሚሽንን ወደ የፈረንሳይ ኢትዮጵያ የጥናት ማዕከል እንዲያድግ ማድረግና የሁለትዮሽ ግንኙነቱ በሁሉም መስክ እንዲጠናከር ተደርጓል።

ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላም የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ጀነራል ጉሌ በኢትዮጵያ ጉብኝት ሲያደርጉ፤ በ1973 ደግሞ ሌላው የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጅ ፖምፒዱ ጉብኝት ግንኙነቱ ወደ ላቀ ደረጃ መሸጋገሩን የሚያመላክት ነበር።

በደርግ ዘመነ መንግስትና በመጀመሪያዎቹ የኢህዴግ ሁለት 10 የስልጣን ዓመታት ግንኙነታቸው ወጣ ገባ ቢልም እአአ በ2013 የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ፍራንሷ ሆላንዴ በአፍሪካ ህብረት 50ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ለመገኘት ወደ ኢትዮጵያ መምጣቸው ለግንኙነቱ ዳግም መጠናከር መሰረት ጣለ።

ከዚያም የኢትዮጵያው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተደጋጋሚ የስራ ጉብኝት አድርገዋል። የሁለቱ አገሮች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተለይም ሚኒስትሮች ጉብኝቶች ተካሂደዋል።

በአሁኑ ወቅት ሁለቱ አገሮች በመካከላቸው ያለው የኢኮኖሚ ትስስርም እየጎለበተ መምጣቱን ከፈረንሳይ ኤምባሲ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

ፈረንሳይ የትራንስፖርት ቁሳቁሶችና የህክምና መገለገያ መሳሪዎች ወደ ኢትዮጵያ ስትልክ ኢትዮጵያ የግብርና ምርቶችን በተለይም ቡና ትልካለች።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለሶስት ሺህ ዜጎች የስራ እድል የፈጠሩ 30 የፈረንሳይ ኩባንያዎች አሉ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከአምስት ወራት በፊት በአውሮፓ በተለያዩ አገሮች ጉብኝት ሲያደርጉ ከጎበኟት አገር መካከል ፈረንሳይ አንዷ ስትሆን ከፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር በትብብር በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ይታወቃል።

ከነዚህም መካከል በአለም አቀፍ መድረክ አንድ በሚያደርጓቸው አጀንዳዎ፣ በጸረ ሸብር፣ በአየር ንብረትና በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስት (ኢጋድ) በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል።

ፈረንሳይ በኢትየጵያ በሚገኘውን ኤምባሲዋን ለጉብኚዎች ክፍት ለማድረግ፣ በዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገበውን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ለማደስ የሚያስችል የገንዘብና የባለሙያ እገዛና ድጋፍ ለማድረግ ሌላው ከስምምነት ከደረሱባቸው ነጥቦች መካከል ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም