በመካከለኛው አዋሽ በመስኖ ከሚለማው መሬት ግማሽ ያህሉ በአፈር ጨዋማነት ተጠቅቷል

90

አዳማ መጋቢት 3/2011 በመካከለኛው አዋሽ በመስኖ ከሚለማው 16 ሺህ ሔክታር መሬት ውስጥ ግማሽ የሚሆነውን በአፈር ጨዋማነት የተጠቃና ተገቢው ምርት የማይገኝበት መሆኑን የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ብሄራዊ የአፈር ምርምር ማስተባበሪያ በሆነው በወረር ግብርና ምርምር ማዕከል የአፈር ለምነትና ጤንነት ተመራማሪ አቶ አሸናፊ ወርቁ እንደገለጹት በመካከለኛው አዋሽ በባለሃብቶችና በከፊል አርሶ አደሮች በመስኖ ከሚለማው መሬት 46 በመቶው በአፈር ጨዋማነት የተጠቃ ነው ።

የችግሩ ዋናው መንስዔ ለውሃው አይከፈልም በሚል ግድየለሽነት ከመጠን በላይ ውሃ ለመስኖ ልማት መጠቀም  መሆኑን ያስረዱት ተመራማሪው፣ በተለይ መሬት ተከራይተው የሚያለሙ ባለሃብቶች በአንድና በሁለት ዓመት የተሻለ ምርት ለማግኘት እንጂ፤ ስለመሬቱ ዘላቂ ደህንነት አይጨነቁም ሲሉ ወቅሰዋል ።

ማዕከሉ የአፈር ጨዋማነት የሚያስከትለውን የምርት መቀነስ ችግር ለመፍታት ያካሄዳቸው ምርምሮች ውጤታማ እየሆኑለት መምጣታቸውን ተማራማሪው ገልጸዋል።

በአንድ በኩል የአፈር ጨዋማነትን ተቋቁመው የተሻለ ምርት የሚሰጡ የቆላ መስኖ ልማት የሰብል ዝርያዎችን በምርምር ማውጣትና የተመሰከረላቸው ዝርያዎችን ከውጪ በማስገባት በሌላ በኩል ደግሞ የተጠቃውን አፈር በማጠብ ፣ በማጠንፈፍ ፣ በጂፕሰንና በተፈጥሮ ቅጠሎች በማከም ወደ ምርታማነት እንዲመለስ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የማዕከሉ የአፈር ጨዋማነትን ተቋቁመው የተሻለ ምርት የሚሰጡ በምርምር ያወጣቸው አራት የሳር ፣ ሁለት የቅጠላቅጠል ፣ ሁለት የስንዴ ፣ ሶስት የጥጥና  ሁለት የሩዝ ዝርያዎችን በአካባቢው ለሚገኙ ባለሃብቶችና ከፊል አርብቶ አደሮች አድርሷል።

በተጨማሪም የአፈር ጨዋማነት የሚቋቋሙ ገብስ ፣ ማሽላና ኪነዋ የመሳሰሉት ስድስት የሰብል ዝርያዎች ከውጪ በማስገባትና በማላመድ ለተጠቃሚው እያደረሰ መሆኑን አቶ አሸናፊ ተናግረዋል።

በማዕከሉ የመስኖ ልማት ተመራማሪ አቶ ጀማል መሐመድ በበኩላቸው አሁን በመስኖ ልማት ዘርፍ የሚታየው ቅጥ ያጣ የውሃ አጠቃቀም ነገ የግጭትና የድርቅ ምንጭ ስለሚሆን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከመጠን በላይ አሁን የምናባክነው ውሃ የእርሻ ማሳዎቻችን በጨዋማነት ተጠቅተው ከምርታማነት ውጭ እንዲሆኑና በውሃ እጥረት ወደ ግጭት  እንዳይከሰት ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ መክረዋል።

ውሃ በሒደት እያለቀ የሚሄድ ሀብት በመሆኑ ተለክቶና ተመጥኖ ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል ያሉት የዘርፉ ተመራማሪ፣  የመስኖ ውሃን መጥኖ መጠቀምና የተረፈውን ውሃ ተመልሶ ወደ መጣበት ምንጭ እንዲገባ የሚያደርግ የምርምር አሰራር እየተዋወቀ ነው ።

ማዕከሉ በተለያዩ በመስኖ የሚለሙ የሰብል ዓይነቶች ላይ የውሃ ልኬት መጠን የሚወስን ምርምር ማድረጉን አቶ ጀማል ገልጸው፣ ስንዴን በመስኖ ለማልማት በጥቁር አፈር በየ10 ቀኑ 100 ሚሊ ሜትር በአሸዋማ አፈር ደግሞ በየአምስት ቀናት 75 ሚሊ ሜትር ውሃ ማጠጣት በቂ መሆኑን አስረድተዋል።

የጥጥ ልማት ለማካሄድ ደግሞ በየሁለት ሳምንቱ 75 ሚሊ ሜትር ውሃ ማጠጣት በቂ በመሆኑ አልሚዎች እንዲተገብሩት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በአፋር ክልል በወረር አካባቢ በግብርና ልማት ላይ የተሰማሩት ባለሃብት አቶ ደምለው ገበየሁ በሰጡት አስተያየት በአካባቢው የአፈር ጨዋማነት ልዩ ትኩረት አግኝቶ ካልተሰራበት በምርታማነት ላይ የሚያሳድረው ተፅእኖ የከፋ ይሆናል።

ባለፈው ዓመት በ76 ሔክታር መሬት ላይ የዘሩትን ጥጥ በአፈር ጨዋማነት መጥፋቱን ያስታወሱት ባለሀብቱ፣ ማዕከሉ ጥረቱን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

የአዋሽ ተፋሰስ ልማት ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ አበጀ መንገሻ እንዳሉት ከሆነ ውሃን ከሚጠቀሙበት በላይ የሚይዙና የተረፋቸውን መልሰው በማይለቁ ተቋማት ላይ ቁጥጥር በማድረግና እርምጃ ለመውሰድ ጨዋማነትን ለመቀነስ አስተዋፅኦ ያበረክታል የሚል ሃሳብ እንዳላቸው ገልጸዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም