የወጣቶችን ተጠቃሚነት ተቋማዊ ለማድረግ የምክር ቤት አባላት እገዛ ያስፈልጋል

94

አዳማ መጋቢት 2/2011 የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ተቋማዊ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የምክር ቤት አባላት አጸንኦት ሰጥተው ሊያግዙ እንደሚገባ የሴቶች ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ጠየቀ።

የወጣቶች ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ተቋማዊ ለማድረግ ከፌደራልና ክልል የህዝብ ተወካዮች ቋሚ ኮሚቴ አመራሮችና አባላት ጋር ለመምከር የተዘጋጀ የሁለት ቀናት መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

በሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ህይወት ኃይሉ በእዚህ ወቅት እንደገለጹት ሁሉን አቀፍ የወጣቶች ፖሊሲ ተቀርፆ እየተሰራ ቢሆንም የሚፈለገው ውጤት አልመጣም።

የሀገሪቱን የእድገት ደረጃ መሰረት በማድረግ የወጣቶችን ፍላጎት በተሟላ መልኩ ምላሽ ለመስጠት ቢሰራም ክፍተቶች መኖራቸውን አመልክተዋል።

የሚታዩ የአሰራር፣ የመዋቅር፣ የአፈጻጸምና የቅንጅት ችግሮችን በመፍታት ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑንም  አስታውቀዋል።

ለእቅዱ ስኬት የህግ አውጪው፣ አስፈጻሚው፣ የህብረተሰቡ፣ የወጣቱ፣ የአጋር አካላትና የባለሀበቱ ርብርብ አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

ወጣቶች በአገራቸው የለውጥ ጉዞ ትርጉም ያለው ውጤት እንዲያስመዝገቡና ከውጤቱም ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ ቅንጅታዊ አሰራር መዘርጋት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

መድረኩም ወጣቶችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ምክር ቤቶች አጸንኦት ሰጥተው እንዲያግዙ ለማድረግ፣ በአፈፃጸም በሚገጥሙ ችግሮች ላይ ለመምከርና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ መዘጋጀቱን ነው የገለጹት።

በእቅዱ ተፈጻሚነት ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሚያደርጉት ክትትል ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ወይዘሮ ሕይወት ጠይቀዋል።

በሚኒስቴሩ የወጣቶች ንቅናቄና ተሳትፎ ዳይሬክተር አቶ ማትያስ አሰፋ በበኩላቸው ሚኒስቴሩ የወጣቶችን ማህበራዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በወጣቶች የልማትና የለውጥ ስትራቴጂ ፓኬጅ ትግበራ ሂደት ካጋጠሙ ችግሮች መካከልም በተቋማት መካከል አለመናበብ፣ የተግባርና የኃላፊነት ድግግሞሽ እንደሚገኙበት ገልጸዋል።

የሚመለከታቸው ሴክተር መስሪያ ቤቶች የወጣቶችን ጉዳይ አካቶ ከመስራት አንፃር የአመራር ቁርጠኝነት ማነስና ሌሎችም ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመው እነዚህ ችግሮች እንዲቃለሉ የምክር ቤት አባላት ግፊት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ጌታቸው መለስ  ወጣቱን ማዕከል ያላደረገ ሥራ አገርን ሊለውጥ ስለማይችል በጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራና የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያስተባብር ኮሚቴ ሊቋቋም እንደሚገባ ገልጸዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው መድረክ የኢትየዽያ ወጣቶች የልማትና የለውጥ ፓኬጅ ሰነድ፣ ብሔራዊ የወጣቶች ጉዳይ ማካተቻ መመሪያ፣ እንዲሁም የወጣቶች ስብዕና ልማት ማዕከላት አገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ ላይ ውይይት እንደሚካሄድ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም