የአምቦ ዩኒቨርስቲ አካል ጉዳተኞችና የጎዳና ተዳዳሪዎች ለማቋቋም ድጋፍ እያደረገ ነው

42

አምቦ መጋቢት 2/2011 የአምቦ ዩኒቨርስቲ ራሳቸውን ችለው እንዲቋቋሙ በማህበረሰብ አገልግሎት በኩል ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አካል ጉዳተኞችና የጎዳና ተዳዳሪዎች ገለጹ።

ዩኒቨርስቲው በተያዘው ዓመት ሰባት ሚሊዮን ብር በጀት መድቦ የማህበረሰብ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አስታውቋል።  

በአምቦ ከተማና የአካባቢው የሚገኙ አስተያየት ሰጪው እንዳሉት የአምቦ ዩኒቨርስቲ በሚሰጠው የማህበረሰብ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል።

ከተጠቃሚዎች መካከል አቶ ደረጀ ሰይፉ በዩኒቨርስቲው ባገኙት የሙያ ስልጠና በአካል ጉዳተኞች መሳሪያ ጥገና ስራ ላይ ሊሰማሩ እንደቻሉ ተናግረዋል።

ከስልጠናው በተጨማሪም ከግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር አገናኝቷቸው አካል ጉዳተኝነታቸው ከመስራት ሳያግዳቸው በሚያገኙት ገቢ ራሳቸውን እያስተዳዳሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በገንዘብ አያያዝ ስልጠና መውስዳቸው ወጪና ገቢያቸውን ለማመጣጠንና  የቁጠባ ባህላቸውን ለማሳደግ እንደረዳቸው አመልክተዋል።

የአካል ጉዳተኛዋ ወይዘሪት ጽጌ ኩመላ በበኩሏ ዩኒቨርሲቲው  የስልጠና፣ የኮምፒውተርና የማተሚያ ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ በገቢ ማስገኛ ስራ መሰማራቷን ተናግራለች።

ወደ ስራ መሰማራቷ ከጠባቂነት ለመላቀቅ እንደረዳት የገለጸችው ወጣት ጽጌ ዩኒቨርስቲው ባመቻቸላት ነፃ የትምህርት   እድል ተጠቃሚ መሆኗን ጠቅሳለች።

ከጊንደበረት ወረዳ ወደ አምቦ ከተማ በመምጣት በጎዳና ተዳዳሪነት ይኖር የነበረው ወጣት ቶሎሣ ፈዬራ  በበኩሉ ዩኒቨርሲቲው  ከጎዳና አንስቶ ስልጠና በመስጠትና የ2 ሺ 500 ብር ድጋፍ በማድረግ በሊስትሮ ስራ እንዲሰማራ እንዳደረገው ተናግሯል፡፡

ከሶስት ዓመት በፊት ያቋረጠውን ትምህርቱንም መጀመር በመቻሉ መደሰቱን አመልክቷል።

ወጣቱ ከሚያገኘው ገቢ በሳምንት 50 ብር ዕቁብ እየጣለ መሆኑንና በስራ  ውጤታማ እንዲሆን ዩኒቨርሲቲው በምክር እያገዘው ነው።

በዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ብዙነሽ ሚደግሳ ከመማር ማስተማር ስራ በተጓዳኝ የአካባቢውን ህብረተሰብ የሚጠቅሙ አገልግሎቶች እየሰጡ እንደሚገኙ  ተናግረዋል።

ዩኑቨርሲቲው ነጻ የህግ አገልግሎት፣ ችግረኛ ሴቶችን በማደራጀት በገቢ ማስገኛ ስራዎች እንዲሰመሩና ለአርሶ አደሩ የሙያ ድጋፍ ይገኙበታል፡፡

በአሁኑ ወቅት የማህበረሰብ አገልግሎት ስራውን ለማጠናከር 7 ሚሊዮን ብር ተመድቦ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው ከዚህም ሱስ ውስጥ ያሉ ሰዎችን ለመደገፍ የማገገሚያ ማዕከል ለመገንባት የቦታ ጥያቄ ለአምቦ ከተማ አስተዳደር አቅርበው ምላሽ እየተጠበቀ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም