የበሰቃ ሀይቅ በረከት እንጂ ስጋት ሆኖ አይቀጥልም ተባለ

612

አዳማ  መጋቢት 2/2011በፍጥነት እየተስፋፋ በመምጣቱ የመተሀራ ከተማ የህልውና ስጋት ሆኖ የቆየው የበሰቃ ሐይቅን ከጥፋት ወደ ልማት ለማሸጋገር የተጀመረው ጥረት ውጤታማ መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

የመተሀራ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ በበኩላቸው በሀይቁ ዙሪያ የነበረው ስጋት በመቃለሉ ባለሃብቶች ልማታዊ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የበሰቃ ሀይቅ በ1966 ዓም በትንሽ ቦታ መፍለቅ እንደጀመረና ባለፉት 45 ዓመታት በፍጥነት እየተስፋፋ መጥቶ በነዋሪዎቹ ዘንድ የመተሀራ ከተማን ሊያጥለቀልቃት ይችላል የሚል ስጋት አሳድሮ መቆየቱን ከከተማው የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል ።

ሀይቁ እስከ 2004 ዓም በነበረው ጊዜ ውስጥ 1ሺህ 278 ሔክታር መሬት በመሸፈን የወጣቶች ማዕከል፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣የጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ፣ የከብት ማድለቢያዎች፣ የመንግሥትና የግል መኖሪያ ቤቶች በማፈራረስ በርካቶች ማፈናቀሉን በጽህፈት ቤቱ የኮሙኒኬሽን ባለሙያ አቶ ገዛሊ ሀሰን ገልጸዋል።

አሁን ግን የውሃ ማውረጃ ቦይ ተከፍቶለት ወደ አዋሽ ወንዝ በማቀላቀል እንዲተነፍስ በመደረጉ የከተማው ስጋት መቃለሉን ተናግረዋል።

የመተሀራ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ ሃልኮ ፈንታሌ በበኩላቸው ሀይቁ በርካቶችን ያፈናቀለና ወደ ከተማዋ በመጠጋት ስጋት ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም፤ አሁን ግን ወደ አዋሽ ወንዝ በማተንፈስ ሕዝቡ እፎይታ ማግኘቱን አስረድተዋል።

በአካባቢው ለ600 ሰዎች የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታና ካርታና ፕላን ተሰጥቶ እንደነበርና በሀይቁ መስፋፋት ምክንያት አካባቢው በውሃ በመጠቃቱ  መስተጓጎሉን ከንቲባዋ ተናግረዋል።

በከተማዋ በበሰቃ ወንዝ ይጠቃል ተብሎ ይሰጋ የነበረው ቀጠና 6 በተባለው አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች ከቦታው ለማስነሳት የነበረው እቅድም አሁን በተፈጠረው የሃይቁ አንፃራዊ መቀነስ ምክንያት ባሉበት እንዲቆዩና ተረጋግተው መደበኛ ኑሮአቸውን እንዲመሩ ተደርጓል።

ሀይቁ በአሁኑ ወቅት ከስጋት ተላቅቆ የከተማዋ ውበትና የልማት ምንጭ መሆን በሚችልበት ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ከንቲባዋ፣ ባለሃብቶች በሀይቁ ዙሪያ የመዝናኛ ማእከላትን በመገንባት ለቱሪዝም እድገት አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በመተሀራ ከተማ 02 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ውብሸት መስፍን በሰጡት አስተያየት በአሁኑ ወቅት በመንግስት እገዛ ነዋሪው ከበሰቃ ወንዝ ስጋት እፎይታ አግኝቷል ።

ሐይቁ መተንፈሻ ስለተሰራለት ከክረምት በስተቀር በበጋ ወራት የሚያሰጋ ነገር አለመኖሩን አቶ ውብሸት ገልጸው፣ እንዲያውም ቄጤማ ማብቀል መጀመሩንና ዓሳና አዞ በስፋት እንደሚታዩበትም ተናግረዋል።

የበሰቃ ሀይቅ በአግባቡ ከለማ እንደ ሀዋሳና ባህርዳር ከተማዋን ሳቢ የመዝናኛ ከተማ ማድረግ ይቻላል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል ።

የበሰቃ ሀይቅ ውሃ ወደ አዋሽ ወንዝ መለቀቁ በመካከለኛውና በታችኛው አዋሽ ተፋሰስ ነዋሪዎችና በልማቱ ላይ ተፅእኖ ይኖረው እንደሆን የአዋሽ ተፋሰስ ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ አቶ አበጀ መንገሻ ተጠይቀው በሰጡት መልስ ከሀይቁ እየተመጠነ ወደ አዋሽ የሚለቀቀው ውሃ የሚያስከትለው ጉዳት የለም።

እንዲያውም የሃይቁ ውሃ በየጊዜው ጥራቱ እየተሻሻለ በመምጣቱ ለመስኖ ልማት አገልግሎት የሚውልበት አማራጭ እየተፈለገ በመሆኑ ከአሁን በኋላ የበሰቃ ሀይቅ በረከት እንጂ ስጋት ሆኖ አይቀጥልም ብለዋል።

በወረር ግብርና ምርምር ማዕከል የዘርፉ ተመራማሪ አቶ አሸናፊ ወርቁ እ የበሰቃ ሀይቅ ውሃ ጥራት እየተሻሻለ መምጣቱንና በሒደት ለመስኖ ልማት መዋል እንደሚችል በጥናት መረጋገጡን አስረድተዋል።

ከአዲስ አበባ እስከ ታችኛው አዋሽ አፍአምቦ ድረስ በዓመት ለአራት ጊዜ የአዋሽ ወንዝ የውሃ ጥራት ናሙና እንደሚወሰድ አስታውሰው፣ የሀይቁ የውሃው የጥራት መጠን ከ7 ነጥብ 4 ዴሲ ሳይመን ወደ  3ነጥብ 2 ዴሲ ሳይመን በመቀነስ መሻሻል እያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።