ኢትዮጵያ የእናቶችና ህጻናት የጤና አገልገሎት ጥራትን ለማሻሻል ከተለያዩ አገራት ጋር እየሰራች ነው

595

አዲስ አበባ መጋቢት 2/2011 ኢትዮጵያ የእናቶች፣ የህጻናትና ጨቅላ ህጻናት ጤና አጠባበቅና አገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል ከተለያዩ የዓለም አገሮች ጋር በጥምረት እየሰራች መሆኑን ጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

ከነገ ጀምሮ ለተከታታይ ሶስት ቀናት የእናቶች፣ የህጻናትና ጨቅላ ህጻናት ጤና አጠባበቅና አገልግሎት ጥራትን በሚመለከት የሚካሄደውን ጉባኤ አስመልክቶ ሚኒስቴሩ መግለጫ ሰጥቷል።

በሚኒስቴሩ የጤና አገልግሎት ጥራት ዳይሬክተር ዶክተር ህሊና ታደሰ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የእናቶች፣ ህጻናትና የጨቅላ ህጻናትን ሞት በመቀነስ ረገድ በርካታ ስራዎችን እያከናወነች ትገኛለች።

አገሪቱ በጤናው ዘርፍ በተለይም በእናቶችና በጨቅላ ህጻናት ዙሪያ የአገልግሎት ጥራትን ተደራሽ ለማድረግ ከተለያዩ የዓለም አገሮች ጋር በጥምረት እየሰራች መሆኑን አመልክተዋል።

በጉባኤው ኢትዮጵያ በዘርፉ ያስመዘገበቻቸውን ውጤቶችና በመከናወን ላይ የሚገኙ ተግባራትን የሚዳስስ ጽሁፍ ይቀርባል ነው ያሉት።

የተገልጋዩ ቅሬታ የሆኑና ያልተፈቱ ችግሮችንም እንዲሁ በማንሳት መፍትሄ እንዲያገኙና የተሻለ አሰራር እንዲዘረጋ ለማስቻልም በችግሮች ላይ ያተኮረ ውይይት እንደሚደረግ በመጠቆም።

በተጨማሪም የጉባኤው ተሳታፊ አገሮችም እንዲሁ የየራሳቸውን ተሞክሮ በማቅረብ ሰፊ የልምድ ልውውጥ የሚደረግበት መድረክ እንደሆነም አክለዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ አሁን ካሉት 10 አባል አገሮች በተጨማሪ 15 አገሮች በጉባኤው እንደሚሳተፉ ገልጸው በአጠቃላይ ከ25 አገሮች የተወጣጡ ከ250 በላይ ባለሙያዎች የሚሳተፉበትና በቀጣይም ቅንጅታዊ አሰራራቸውን ለማጎልበት አቅጣጫ የሚያስቀምጡበት ነው።

ጉባኤው ኢትዮጵያ በዘርፉ የጀመረችውን የተሻለ እንቅስቃሴ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያደርስና በእናቶችና ጨቅላ ህጻናት የጤና አገልግሎት ጥራት ላይ የሚነሱ ችግሮችን በመቅረፍ አለም አቀፍ ትስስርን የሚፈጥር እንደሆነም ዶክተር ህሊና አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ የዓለም የጤና ድርጅት የእናቶች፣ የህጻናትና ወጣቶች ፕሮግራም አስተባባሪ ዶክተር አዝማች ሃዱሽ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በዘርፉ ከሚሰሩ አገሮች ጋር እየሰራች በመሆኑ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ አስችሏታል።

ለዚህም በአገር አቀፍ ያሉ ሆስፒታሎችና የጤና ተቋማት ቅንጅታዊ አሰራራቸውን እንዲያዳብሩና የእናቶችና ጨቅላ ህጻናት የጤና አገልግሎት ጥራትን ማስጠበቅ ላይ ሰፊ ውይይት ይደረጋል።

የአገልግሎት ጥራትን በሚመለከት የአመራር ብቃት፣ ከጉባኤው የተገኙ ግብአቶችን ወደ ተግባር የማስገባትና ከወረዳ ጀምሮ ያሉ የጤና ተቋማትና ባለሙያዎች የሚማማሩበትና ልምድ የሚለዋወጡበትን አቅጣጫዎች ማስቀመጥ የጉባኤው አጀንዳ እንደሆነ ጠቁመዋል።  

ጉባኤው እ.ኤ.አ በ2017 ሲጀመር ማላዊና ታንዛኒያ የመጀመሪያውንና ሁለተኛውን ጉባኤ ያዘጋጁ ሲሆን የዘንድሮውን ጉባኤ በአዲስ አበባ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) ይካሄዳል።