አደጋ የደረሰበት አውሮፕላን የመረጃ ሳጥን ተገኘ

774

አዲስ አበባ  መጋቢት 2/72011 ትናንት ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ሲበር የመከስከስ አደጋ የደረሰበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን የመረጃ ሳጥን (black box) ተገኘ።

የአየር መንገዱ ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አስራት በጋሻው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የመረጃ ሳጥኑ መገኘት የምርመራ ሂደቱን ያቀላጥፋል።

በበረራ ወቅት የአውሮፕላኑ የተለያዩ መሣሪያዎች እንቅስቃሴ መዝግቦ የሚያስቀረውን (DFDR) ወይም የመረጃ ሳጥን (balck box) አደጋው በደረሠበት ቦታ መገኘቱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታውቋል።

የመረጃ ሳጥኑ መገኘት ለአደጋው መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ ለተባሉ ምክንያቶች በቅርብ ጊዜ ውስጥ ምላሽ እንዲገኝ እንደሚያደርግ የአቪዬሽን ባለሙያዎች በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።

በተጨማሪም በበረራ ወቅት የአብራሪዎቹን እና በአውሮፕላኑ ውስጥ ድምጾችን የሚቀርጸው መሣሪያ (CVR)  መገኘቱንም አየር መንገዱ ገልጿል።

የበረራ ቁጥሩ ኢቲ 302 የሆነው ይህ አውሮፕላን 149 መንገደኞችንና 8 የበረራ ሰራተኞችን አሳፍሮ በረራ ከጀመረ ከስድስት ደቂቃ በኋላ በመከስከሱ በውስጡ የነበሩ 157 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል፡፡