የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሙስናን ለመከላከል ግልጽ የሆነ አሰራር መከተል አለባቸው

91

አዲስ አበባ  መጋቢት 2/2011 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሙስናን ለመከላከል ግልጽ የሆነ አሰራርን ሊከተሉ እንደሚገባ ተጠቆመ።   

የፌዴራል የሥነ-ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመሆን ጉባኤ አካሂዷል።   

በጉባኤው ላይ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች፣ መምህራን የተማሪ ተወካዮችና የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።  

በጉባኤው በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሙስና፣ የሥነ -ምግባርና የመልካም አስተዳደር ችግር ዙሪያ የሚያጠንጥን የጥናት ውጤትም ቀርቧል።  

ከአዲግራት ዩኒቨርስቲ የተወከለሉት የጥናቱ አቅራቢ አቶ ግርማይ ተክሉ እንደተናገሩት፤ ጥናቱ በአስር ዩኒቨርሲቲዎች ላይ የተካሄደ ሲሆን አዲስ አበባ፣ ጅማ፣ ሀዋሳ፣ አክሱም ድሬዳዋና ደብረ ብርሃን ጥናቱ ከተካሄደባቸው መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።      

በተደረገው ጥናት በተማሪዎች አገልግሎት አሰጣጥ፣ ተማሪዎች የሚማሩበትን ተቋም ንብረት በአግባቡ አለመጠቀም፣ ከቅጥርና እድገት ጋር ተያይዞ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በተለይ ግዥ ላይ ከፍተኛ ሙስና እንደሚታይ የገለጹት አቶ ግርማይ፤ በአግባቡ ጨረታ አለማውጣት፣ በጥቅም ትስስር ለአንድ ተጫራች ብቻ ደጋግሞ መስጠት፣ የግንባታና ማስፋፋያ ሥራዎች ከፍተኛ በጀት መያዝ በጥናቱ የለያቸው ችግሮች እንደሆኑ ተናግረዋል።

እንደ አቶ ግርማይ ገለጻ፤ በጥናቱ የተለዩ ችግሮችን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለመፍታት የአሰራር ግልጽነትና ተጠያቂነት ማስፈን ይጠበቅባቸዋል። 

የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሥነ-ምግባርና የጸረ ሙስና ተቋም ቅጥርን ጨምሮ ከተጽዕኖ ነጻ መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።    

በትምህርት ተቋማቱ ውስጥ ያለው የሥነ-ምግባር መመሪያ ወደ ተግባር ሊቀየር እንደሚገባ ያመለከቱት አቶ ግርማይ የቅጥርና የእድገት አሰራሩ ለሁሉም ወጥ በሆነ መንገድ ተግባራዊ መደረግ አለበት ይላሉ። 

የፌዴራል የሥነ-ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽነር አየልኝ ሙሉዓለም በበኩላቸው የልማትና የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አጀንዳን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ሙስናን የሚጠሉ፣ ሥነ-ምግባራቸውን የጠበቁ ዜጎች ለማፍራት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጠይቀዋል።

''የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ራሳቸውን ከሙስናና ብልሹ አሰራር ጽዱ ማድረግ ይኖርባቸዋል'' ብለዋል። 

ትራንስፓረንሲ ኢኒሼቲቭ ኢትዮጵያ በኮሚሽኑ ድጋፍ በኮንስትራክሽን ዘርፍ በ14 ዩኒቨርስቲዎች ባካሄደው ጥናት የ2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር የማስፋፋያ ግንባታ ፕሮጀክት አፈጻጸም ችግሮች መለየቱን ተናግረዋል።

ግንባታዎች በአማካይ በ103 በመቶ መራዘም፣ በዋጋም ከ10 እስከ 25 በመቶ ጭማሪ እንደሚታይ የጥናት ውጤቱ አመላክቷል።

አቶ አየልኝ እንደሚሉት፤ ከገንዘብ ብክነቱ ባለፈ ህንጻዎች በወቅቱ አለመጠናቀቃቸው ለትምህርት ስርዓቱ መቀላጠፍ ማነቆ ሆነዋል።

በዩኒቨርሲቲዎች የሚታዩ የሙስናና መልካም አስተዳደር ችግሮችን በጥናት በመለየት በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ኮሚሽኑ ከከፍተኛ ተቋማት ጋር በመተባበር ዘላቂ እልባት ለማምጣት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም