የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ማሻሻያ ያደረገበትን የእምቦጭ አረም መሰብሰቢያና መፍጫ ማሽን አስተዋወቀ

117

ጎንደር መጋቢት 2/2011 የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ማሻሻያ ያደረገበትን የእምቦጭ አረም መሰብሰቢያና መፍጫ ማሽን በቅርቡ ለማስረከብ መዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከአጋር አካላት ጋር በመሆን የቴክኖሎጂ ፈጠራ ማሻሻያ ያደረገበትን ማሽን ትናንት በጣና ሐይቅ ጎርጎራ ወደብ ለተለያዩ አካላት አስጎብኝቷል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የኢንዱስትሪ ትስስርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መስፍን እንደተናገሩት ከዚህ ቀደም በማሽኑ የአረም መሰብሰቢያ አካል ላይ የታየውን ችግር በማሻሻል በተሻለ ብቃት ሰርቶታል፡፡

ማሽኑ በአሁኑ ወቅት ወደ አገር ውስጥ ገብተው በሐይቁ የአረም ማስወገድ ሥራ ከተሰማሩት ማሽኖች ጋር ሲነጻጸር በአራት እጥፍ አቅም አለው ብለዋል፡፡

በዚህም ማሽኑ በሰዓት 444 ኩንታል የእምቦጭ አረም ከሐይቁ ላይ የመሰብሰብ አቅም እንዳለውም አስረድተዋል፡፡

ከኢንተርፕራይዞችና ከጎንደር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ጋር በመቀናጀት የተሰራው ማሽን ከጄኔሬተር በስተቀር ሁሉም አካላት በአገር ውስጥ ጥሬ ዕቃ ብቻ የተሰሩ ናቸው፡፡

ማሽኑ 2 ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበት የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፣ የመጨረሻ ደረጃ የሙከራ ፍተሻውን በማጠናቀቅ በአጭር ቀናት ውስጥ ለሚመለከተው አካል ለማስረከብ ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

ማሽኑ በተጨማሪም የተሰበሰበውን አረም ፈጭቶ ከሐይቁ የሚያስወግድ መሣሪያም እንደተገጠመለት ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

በማሽኑ ተፈጭቶ የተወገደውን አረም ለስድስት ወራት በሐይቁ ውስጥ በማቆየት በተደረገው ጥናት አረሙ ዳግም የመብቀል ባህርይ እንዳላሳየ አስረድተዋል፡፡

የጎንደር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ምክትል ዲን አቶ ካለአምላክ አበበ በበኩላቸው ማሽኑ በሙከራ ሂደቱ የተሻለ ብቃት እንዳለው መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡

ማሽኑ የቴክኖሎጂ ፈጠራን ለማጎልበት አቅም የፈጠረና አገር በቀል ንድፈ ሃሳብን ወደ ተግባር በማሸጋገር የላቀ ዕውቀት የተመዘገበበት ነው ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል የአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን የጣና ሐይቅ ሥርዓተ ምህዳር ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ መዝገቡ ዳኘው  ዩኒቨርሲቲው የሰራው ማሽን  በአገሪቱ ፈር ቀዳጅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሐይቁ ላይ የተከሰተውን አረም ለማስወገድ  የኅብረተሰቡ የጉልበት ተሳትፎ መተኪያ እንደሌለው አመልክተዋል፡፡

የኅብረተሰቡን ተሳትፎ የሚያግዙ ሦስት ማሽኖች ከውጭ ገብተው በአረም ማስወገድ ሥራው በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡

ዩኒቨርሲቲው ያሰራው ማሽን የፍተሻና የሙከራ ሂደት አልፎ ሲጠናቀቅ ባለሥልጣኑ ተረክቦ ወደ ሥራ ለማስገባት መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል፡፡

አረሙ የሀይቁ አዋሳኝ በሆኑት በደቡብና በማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች በሚገኙ ስድስት ወረዳዎችና 21 ቀበሌዎች መስፋፋቱን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም