ቻይና የቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን በረራን ላልተወሰነ ጊዜ አገደች

86

አዲስ አበባ መጋቢት 2/2011 ቻይና በኢትዮጵያ የተከሰከሰውን ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋ ተከትሎ ተመሳሳይ አውሮፕላኖች ላልተወሰነ ጊዜ በረራ እንዳያደርጉ አገደች።

የእንግሊዙ የዜና ምንጭ ቢቢሲ የቻይና የአቪየሽን ተቆጣጣሪ ባለስልጣንን ጠቅሶ እንደዘገበው የቻይና የአየር መንገዶች ከኢትዮጵያው የአውሮፕላን አደጋ በኋላ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች በረራ እንዳያድርጉ አግዳለች።

በኢትዮጵያ ትላንት ከደረሰው የመከስከስ አደጋ በተጨማሪ ከጥቂት ወራት በፊት ላዮን ኤየር የተሰኘ የኢንዶኔዚያ አየር መንገድ ንብረት የሆነ ተመሳሳይ ሞዴል ከመሬት ከተነሳ ከ18 ደቂቃ በኋላ ተከስክሶ የ189 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል።

የበረራ ባለሙያዎች በኢትዮጵያው የተከሰተው የአውሮፕላን አደጋ ከሞዴሉ ጋር ስለመያያዙ ለመናገር ጊዜው ገና መሆኑን እየጠቀሱ ሲሆን ነገር ግን ሁለቱም አደጋዎች ቦይንግ 737 ማክስ 8 ላይ መድረሳቸውና በተነሱ በደቂቃዎች ውስጥ አደጋዎቹ መድረሳቸው ያመሳስላቸዋል ብለዋል።

ቻይና 96 ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች እንዳሏት መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ቦይንግ 737 ማክስ 8 ሞዴል አውሮፕላን እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ2017 ጀምሮ ወደ በረራው የገባ አዲስ ምርት መሆኑ ይታወሳል።

ትናንት ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ሲበር የነበረው ንብረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ቢሾፍቱ አካባቢ መከስከሱ ይታወቃል።

የበረራ ቁጥሩ ኢቲ 302 የሆነው ይህ አውሮፕላን 149 መንገደኞችንና 8 የበረራ ሰራተኞችን አሳፍሮ በረራ ከጀመረ ከስድስት ደቂቃ በኋላ በመከስከሱ በውስጡ የነበሩ 157 ሰዎች ህይወት አልፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም