የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖቹን ከበረራ አገደ

105

 አዲስ አበባ  መጋቢት 2/2011  የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉትን ቀሪ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖቹን ላልተወሰነ ጊዜ ከበረራ ውጪ እንዲሆኑ ማድረጉን ዛሬ ጠዋት አስታውቋል።

አየር መንገዱ ከቦይንግ የገዛቸው አምስት ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ያሉት ሲሆን አንዱ ትናንት አደጋ የደረሰበት መሆኑን የአየር መንገዱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አስራት በጋሻው ዛሬ ለኢዜአ ገልፀዋል።

ከአዲስ አበባ ናይሮቢ ኬኒያ ሲጓዝ የተከሰከሰው የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የ33 አገራት 149 መንገደኞችና ስምንት የበረራ አስተናጋጆችን ይዞ ነበር።

የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅትንና ቦይነግን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ያሉት ኮሚቴ የአደጋውን መንስኤ በዚህ ሳምንት መመርመር እንደሚጀምርም አቶ አስራት ተናግረዋል። 

ከተሳፋሪዎቹ መካከል 32ቱ ኬኒያዊያን ሲሆኑ፤ 17ቱ ኢትዮጵያዊያን ቀሪዎቹ ደግሞ የሌሎች አገራት ዜጎች መሆናቸውን አየር መንገዱ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አስታውቋል።

አደጋው የደረሰበት ትናንት ማለዳ ከቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በተነሳ በስድስት ደቂቃ ልዩነት መሆኑን የተገለጸ ሲሆን የአደጋው መንስኤ እስካሁን አልታወቀም።

ጠቅላይ ሚኒሰትር ዶክተር ዓብይ አህመድን ጨምሮ የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት በደረሰው አደጋ ሀዘናቸወን ገልፀዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ዛሬ ብሄራዊ የሀዘን  ቀን አንዲሆን አውጇል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም