እየተሰጠ ያለው የቋንቋ ስልጠና በታካሚዎችና የህክምና ባለሙያዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ያጠናክራል-የጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ

1947

አዲስ አበባ ግንቦት 22/2010 በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ እየተሰጠ ያለው የኦሮምኛ ቋንቋ ስልጠና ከታካሚዎች ጋር ተግባብተው እንዲሰሩና ጊዜን ለመቆጠብ እንደሚረዳቸው ሰልጣኞች ተናገሩ።

ሆስፒታሉ እየሰጠ ያለው የቋንቋ ስልጠና ለሶስት ወራት የሚቆይ እንደሆነ ተገልጿል።

ሲስተር ሰርካለም ሙላትና የዐይን ህክምና ኦፕቶሜትሪስት እጸገነት ብርሃኔ እንደተናገሩት ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡ አብዛኛዎቹ ታካሚዎች ኦሮምኛ ተናጋሪዎች በመሆናቸውና እነሱ ደግሞ  ቋንቋውን አለመቻላቸው ስለህመማቸው ለመረዳትና አስፈላጊውን ህክምና ለመስጠት አስተርጓሚ ይፈልጉ ነበር።

ይህም ሲሆን የአስተርጓሚውም ሆነ የነሱ ጊዜ ይባክን እንደነበርና አሁን እየተሰጠ ያለው ህክምና ከታካሚ ጋር ተግባብተው ስራቸውን እንዲሰሩ የሚያስችላቸው መሆኑን ያስረዳሉ።

እስካሁን ባለው ሂደት ታካሚ ወዴት መሄድ እንደሚፈልግ ሰላምታና ምን እንደፈለግ ማወቅ መቻላቸውንም ተናግረዋል።

ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ዶክተር ትሁት ተሾመ  ደግሞ እሷ ቋንቋውን በመቻሏ ለሌሎች ቋንቋውን ለማይችሉ ባለሙያዎች ታካሚዎች የሚሉትን በመተርጎም ትረዳ እንደነበር ገልጻለች።

በዚህ ጊዜ ታካሚዎቹ ሃሳባቸውን በግልፅ ማስረዳት እንደሚችሉና የሚሉትን የሚረዳ ባለሙያ በማግኘታቸው ደስታ እንደሚሰማቸው ነው የምትናገረው።

ስልጠናው ቋንቋ ለሚችሉት በመተርጎም የሚያጠፉትን ጊዜ የሚቀንስ፤ ለማይችሉት ደግሞ ታማሚዎችን በደንብ እንዲያስተናግዱ ከማድረጉም ባሻገር ታማሚው በሀኪሙ ላይ ‘ተረድቶኛል’ ብሎ እምነት እንዲጥል ያደርገዋልም ብላለች።

በሆስፒታሉ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት “70 በመቶ የሚሆኑት ታካሚዎች ከኦሮሚያ ክልል የሚመጡ መሆኑን ያሳያል” ያሉት ደግሞ የስልጠናው ዋና አስተባባሪ ዶክተር ቶማስ መኩሪያ ናቸው።

ከነዚህም ውስጥ 30 በመቶው ኦሮምኛ ቋንቋ ብቻ የሚናገሩ በመሆናቸው የህክምና ባለሙያዎች አስተርጓሚ በመፈለግ ስራ ሲሰሩ የጊዜ ብክነት ለመቀነስና ትክክለኛ መረጃን ለማግኘት ስልጠናው መዘጋጀቱን ገልፀዋል ዶክተሩ።

በስልጠናው 120 የህክምና ባለሙያዎች በአራት ክፍሎች እየሰለጠኑ እንደሆነ ገልፀው፤ ስልጠናው የሚሰጠው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኦሮሚኛ ቋንቋ ምሁራን ጋር በመተባበር መሆኑን ተናግረዋል።

ስልጠናው የሚሰጠው ከ5 ሰዓት ተኩል እስከ 6 ሰዓት ተኩል ሲሆን፤ ሰዓቱ የተመረጠው የስራን ሰዓት ላለመሻማት ነው ብለዋል።

ለስልጠናው ከ5 መቶ በላይ ሰልጣኞች ተመዝግበው ለመጀመሪያ ዙር 120 ባለሙያዎች እየሰለጠኑ መሆኑን የተናገሩት ዋና አስተባባሪው በቀጣይ ዙር የሚቀጥል መሆኑም አብራርተዋል።