በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ ነዋሪዎች ተናገሩ

66

ነቀምቴ መጋቢት 1/2011 በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ የዞኑ ነዋሪዎች ገለጹ።

በዞኑ በሻምቡ ከተማ ዛሬ የሰላምና የልማት ኮንፍረንስ ተካሂዷል፡፡

የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አንዳንድ ነዋሪዎች እንደገለጹት ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ እንሰራለን ብለዋል።

በዞኑ ሆሮ ወረዳ የኮምቦልቻ ጫንጮ ቀበሌ ነዋሪ አባገዳ አዱኛ ዳመሳ እንደተናገሩት በዞኑ ተከስቶ በነበረው የሰላም ዕጦት የልማት ሥራዎች ተቋርጠው እንደነበር አስታውሰዋል። 

አሁን የተገኘውን ሰላም በመጠቀም ሕዝቡ የዞኑን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ ከመንግሥት ጎን እንዲቆም ጠይቀዋል።

ከአገር ሽማግሌዎችና ከሃይማኖት አባቶች ጋር በመሆን ህዝቡ አንድነቱንና ፍቅሩን እንዳይቋረጥ ቅስቀሳና ምክር ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የሆሮ ወረዳ የድድቤ ክስታና ቀበሌ የአባ ገዳዎች አማካሪ አቶ ደበላ ዴካማ በዞኑ የተገኘው ሰላም ዘላቂነት እንዲኖረው ኅብረተሰቡ ድርሻውን መወጣት እንዳለበት ጠይቀዋል።

በዞኑ ባለፉት ሦስት ዓመታት ተቋርጦ የነበረውን ልማት ለማስቀጠል ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን እንዲቆም አሳስበዋል።

የጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ የአሊቦ 01 ቀበሌ ነዋሪ አቶ አብዲሣ ኡርጌሳ  የዞኑን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ ከፍተኛው አመራሩና ኅብረተሰቡ አንድነታቸውን አጠናክረው በጋራ መሰራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መንቀሳቀስ እንደሚገባም አስተያየት ሰጪው ጠይቀዋል።

የአባይ ጮመን ወረዳ የፊንጫአ ከተማ 01 ቀበሌ  የሃይማኖት አባት ሼህ መሐሙድ ሙሳ የዞኑን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ የድርሻቸውን እንደሚያበረክቱ ገልጸዋል።

የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ጋዲሴ ሻሾ በበኩላቸው በዞኑ የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የድርሻዬን እወጣለሁ ብለዋል።

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ በዳሣ ጅንፌሣ የተገኘውን  አንጻራዊ ሰላም በመጠቀም የቀበሌ አደረጃጀት በአዲስ መልክ  ተጠናክሮ ወደ ሥራ መገባቱን አስታውቀዋል።

በዚህም ተቋርጠው የነበሩ የመሠረተ ልማት ሥራዎች መቀጠላቸውን ተናግረዋል።

በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው የዞኑ ህዝብ አንድነቱን  አጠናክሮ የተገኘውን ሰላም አስጠብቆ መሄድ እንዳለበት አሳስበዋል።

የክልሉ መንግሥት የሕዝቡን ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ለመመለስ ቁርጠኛ መሆኑንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም