በተከሰከሰው አውሮፕላን ተሳፋሪዎች የነበሩ በሙሉ ህይወታቸው አልፏል

94

አዲስ አበባ መጋቢት 1/2011 በዛሬው ዕለት የተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ተሳፋሪዎች በሙሉ ህይወታቸው ማለፉ ተገለጸ።

ከአዲስ አበባ ናይሮቢ ኬኒያ ሲጓዝ በምሥራቅ ሸዋ ዞን ጊምቢቹ ወረዳ ላይ የተከሰከሰው የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 የሆነው ቦይንግ 737 የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የ33 አገራት 149 መንገደኞችና ስምንት የበረራ አስተናጋጆችን ይዞ ነበር።

ከተሳፋሪዎቹ መካከል 32ቱ ኬኒያዊያን ሲሆኑ፤ 17ቱ ኢትዮጵያዊያን ቀሪዎቹ ደግሞ የሌሎች አገራት ዜጎች መሆናቸውን አየር መንገዱ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አስታውቋል።

አውሮፕላኑ አደጋው የደረሰበት ዛሬ ማለዳ ከቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በተነሳ በስድስት ደቂቃ ልዩነት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን የአደጋው መንስኤ እስካሁን አልታወቀም።

በአደጋው የሁሉም ህይወት ያለፈ ሲሆን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በአደጋው የተሰማውን ሀዘን በመግለጽ ለሟች ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች መጽናናትን ተመኝቷል።

በተመሳሳይ የኬኒያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በአደጋው የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸው ለአደጋው ሰለባ ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም