የአማራ ክልል ምክር ቤት የምሁራን መማክርት ጉባዔ ማቋቋሚያ ዓዋጅን አጸደቀ

130

ባህር ዳር መጋቢት 1/2011 የአማራ ክልል ምክር ቤት እያካሄደ ባለው 12ኛ መደበኛ ጉባዔ  የክልሉ ምሁራን መማክርት ጉባዔን ለማቋቋም የቀረበውን ዓዋጅ  አጸደቀ።

ምክር ቤቱ ያጸደቀው ዓዋጅ የክልሉን ሁለንተናዊ ልማትና ዕድገት ለማፋጠን የምሁራንን ሚና ለማሳደግ እንደሚያስችል ታምኖበታል።

ምክር ቤቱ በቀረበው ረቂቅ ዓዋጁ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ በአብላጫ ድምፅ አፅድቆታል።

የምክር ቤቱ የሕግ፣ ፍትህና አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አማረ ሰጤ በሰጡት ማብራሪያ የዓዋጁ መውጣት ምሁራን በክልሉ ልማት ላይ የሚያበረክቱትን ተቋማዊ ራዕይ ዕውን ለማድረግ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

ዓዋጁን ማውጣት ያስፈለገውም የክልሉን ሃብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋልና የሕዝቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የምሁራን ድርሻ ወሳኝ ሆኖ በመገኘቱ ነው ብለዋል።

ጉባዔው የራሱ የሆነ ሕጋዊ ሰውነት ያለው፣ መዋቅራዊና ሙያዊ ነፃነቱ የተለየ መሆኑንም አስረድተዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የሕግ አማካሪ አቶ መርሃ ጽድቅ መኮንን ረቂቅ ዓዋጁን ሲያቀርቡ በክልሉ ዘላቂና ሁለንተናዊ ልማት ለማረጋገጥ የምሁራን ሙያዊ እገዛ አስፈላጊ እንደሆነ አብራርተዋል።

ምሁራን ለክልሉ ልማት በተበታተነ መልኩ ምክረ ሃሳብ ከማቅረብ በዘለለ በተደራጀ አግባብ ሲንቀሳቀሱ እንዳልነበረ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።

በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ የሚኖሩ ከ500 የሚበልጡ የክልሉ ተወላጅ ምሁራን በመሰባሰብ በዚህ ዓመት መጀመሪያ የምሁራን መማክርት መስራች ጉባዔ ማቋቋማቸውን ገልጸዋል።

የክልሉ ተወላጅ ምሁራን ወደአንድ መሰባሰባቸው የተደራጀ አቅምና ዕውቀታቸውን በመጠቀም በሚያደርጉት ሙያዊ እገዛ የክልሉን ልማት እንደሚያፋጥነው አስረድተዋል።

በክልሉ የሚታዩትን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ችግሮች በሳይንሳዊ ዕውቀትና ዘዴ በመፍታት ዘላቂ የሆነ ሁለንተናዊ ልማትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ድርሻ አለው ብለዋል።   

ከምሁራን የሚገኘው ሙያዊ ዕገዛም ውጤታማና ዘላቂ ልማት እንዲፋጠን ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ጭምር በመጠቆም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም