የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የተሻሻሉ የዓሣ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ እያቅበ ነው

76

አምቦ  የካቲት 30/2011 ከመደበኛ የእርሻ ስራቸው በተጓዳኝ የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ባቀረበላቸው  የተሻሻሉ የዓሣ ዝርያዎች ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ በምዕራብ ሸዋ ኤጀርሰ ለፎና የቶኬ ኩታዬ ወረዳዎች  አርሶ አደሮች ገልጹ፡፡   

ዩኒቨርሲቲው የአርሶ አደሩንና የሌላውንም ህብረተሰብ  ህይወት ለመለወጥ የሚያግዙ 148 የምርምር ስራዎችን በማካሄድ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

አርሶ አደር በቀለች ብሩ  በኤጀርሰ ለፎ ወረዳ የተሩ ጅንጀም ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ  በአካባቢያቸው የሚያልፍ የወንዝ ውሃ ቢኖርም ለረጅም ዓመታት ሳይጠቀሙበት መቆየታቸውን ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡

የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ዓሣ የሚያረቡበትን ኩሬ አስገንብቶ የዓሣ ዝርያን ካስገባላቸው ወዲህ ግን ከእርሻ ስራቸው በተጓዳኝ በዘርፉ እርባታ  በመሳተፍ ተጨማሪ ገቢ እያገኙ ናቸው፡፡

አርሶ አደሩ እንዳሉት በተያዘው ዓመት ከዓሣ ሽያጭ  ከ35ሺ ብር በላይ ገቢ እንዳገኙ ጠቅሰው እርባታውን አጠናክረው የተሻለ ገቢ ለማግኘት ትኩረት መሰጠታቸውን አመልክተዋል፡፡

ለዚህም  የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው  እንደሚፈልጉ ጠቁመው  ከዓሣ ኩሬው የሚለቀቀው ውሃም ለመስኖ ልማታቸው በመዋሉ ለማዳበሪያ ግዥ የየሚያወጡትን ወጪ ማስቀረት እንዳቻሉም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በዚሁ ወረዳ የጀቢነ ወለገባቱ ቀበሌ አርሶ አደር ደረጄ በቀለ በበኩላቸው የተሻሻለ የዓሣ ዝርያ አግኝተው ማርባታቸው  ውጤታማ እንዲሆኑ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በአካባቢያቸው ዓሣን በባህላዊ መንገድ ከወንዝ ውስጥ ብቻ በማውጣት ይሸጡ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ዩኒቨርስቲው ዘመናዊ የዓሣ ማርቢያ ኩሬና የተሻሻሉ ዝርያዎችን ካቀረበላቸው ወዲህ ግን ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ ገልጸው ባለፉት ዓመታትም ከዓሣ ምርት ሽያጭ ካገኙት ገቢ ያልነበራቸውን ሁለት የእርሻ በሬዎችን መግዛታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ሌላው በቶኬ ኩታዬ ወረዳ የሙቱሉ ቀበሌ አርሶ አደር ሽመልስ ፊሪሣ  እንዳሉት ከዓሣ እርባታ በሚያገኙት ገቢ ተጨማሪ የመኖሪያ ቤት በመስራት ናቸው፡፡

አልፎ አልፎ የሚታየውን የገበያ ትስስር ችግርም መንግስት እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል፡፡

በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የግብርና ትምህርት ክፍል መምህር  ዶክተር ወርቅነህ አበበ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ ብዛት ያላቸው የምርምር ስራዎችን እያካሄደ ነው፡፡

ከእነዚህም በዓሣ ዝርያ ማሻሻል ላይ ምርምር ተካሂዶ ከሁለት ዓመት በፊት አርሶ አደሮች ጋር የደረሰው የምርምር ዘርፍ ተጠቃሽ ነው፡፡

በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው የአርሶ አደሩን ህይወት በሚለወጡና እርሻን ዘመናዊ በሚያደርጉ ስራዎች ላይ ምርምሮችን በመስራት ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል፡፡

መስሪያ ቤታቸው ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የተሻሻሉ የዓሣ ዝርያዎችን ወደ ተለያዩ ወረዳዎች በማሰራጨት ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ  በምዕራብ ሸዋ ዞን የእንስሳት ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ መሣይ እንየው ናቸው፡፡

እስካሁንም በዞኑ 11 ወረዳዎች ማዳረስ መቻሉን አመልክታው በቀጣይነት በሁሉም የዞኑ ወረዳዎች ወደ አርሶ አደሮች ለማድረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አርሶ አደሮች ያነሱትን የገበያ ትስስር ችግርም ለመፍታት ከሆቴሎችና ከሌሎችም አካላት ጋር በመነጋገር ላይ እንዳሉም ጠቅሰዋል፡፡ 

የአምቦ ዩኒቨርሲቲ በተያዘው ዓመት 14 ሚሊየን ብር በሆነ ወጪ 148 የምርምር ስራዎችን በማከናው ላይ መሆኑን አመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም