በትግራይ በምርምር የታገዘ የቀርከሀ ልማት እየተካሄደ ነው

81

መቀሌ የካቲት 30/2011 በትግራይ የቀርከሀ ሀብትን ከጥፋት ለመታደግና ለማስፋፋት በምርምር የታገዘ ልማት መጀመሩን የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

በክልሉ ወደ መጥፋት ደረጃ ላይ የደረሰውን የቀርቅሃ ተክል ለመታደግ ከቻይና የመጡ 13 አይነት የቀርከሀ ዝርያዎችን የማባዛት ሥራ እየተከናወነ መሆኑም ተመልክቷል።

የክልሉ ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ክፍሎም አባዲ ለኢዜአ እንደገለጹት ልማቱን የማስፋፋት ሥራ የተጀመረው ለቀርከሀ ተክል አመቺ በሆኑ ስምንት ወረዳዎች ነው።

በተደፋት፣ ቦረቦርና ወንዝ ዳርቻ እንዲሁም ኩታገጠም መሬቶች ላይ ተክሉን ለማልማት የሚያስችል ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል ።

አቶ ክፍሎም እንዳሉት ለደጋና ቆላማ አየር ንብረት ተስማሚ የሆኑ 13 አይነት የቀርካሀ ተክል ዝርያዎችን ከቻይና በማስመጣት በዘር፣ በችግኝና በቁርጥራጭ መልክ የማባዛት ሥራ እየተከናወነ ነው።

ለእዚህም በባዮ ቴክኖሎጂ ዘዴ በመታገዝ 12 ሚሊዮን ችግኞች መዘጋጀታቸውንም ለአብነት ጠቅሰዋል።

“በክልሉ ለተክሉ አመቺ የሆነ 300ሺህ ሄክታር መሬት አለ” ያሉት ኃላፊው ቀርከሀ የአፈር መከላትን ከመከላከል ባለፈ ለቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁስና ጌጣጌጥ ምርት እንደሚውል ገልጸዋል።

ለአካባቢ ጥበቃና ለገቢ ምንጭም ያለውጥ ጥቅም ከፍተኛ መሆኑን አስታውቀዋል።

ተክሉ የአካባቢ ስነ ምህዳር የመጠበቅና የአፈር ለምነት የመጨመር አቅሙ ከፍተኛ መሆኑን የገለፁት ደግሞ  በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የስነ- አካባቢና የተፈጥሮ ሀብት ተመራማሪና መምህር ፕሮፌሰር እምሩ ብርሃነ ናቸው፡፡

" ቀርከሀ ካርቦን ዳይኦክሳድን የመምጠጥ አቅሙ ከፍተኛ በመሆኑ የአየር ብክለትን ለመከላከል ያለው ድርሻ የጎላ  ነው" ብለዋል ።

በተለይ ከቆዳና ብረታ ብረት ፋብሪካዎች የሚለቀቁ ለጤና ጎጂ የሆኑ ኬሚካሎችን መጥጦ በማስወገድ የተበከለ አካባቢ የማጥራትና የማፅዳት ኃይል እንዳለው ተናግዋል።

"በክልሉ ቆላማ አካባቢዎች ተክሉን ለማስፋፋት በተከዜ ወንዝ ዳርቻ ላይ በመትከል የምርምር ሥራ እየተከናወነ ነው” ያሉት ደግሞ የትግራይ ባዮ-ቴክኖሎጂ ማዕከል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የዘርፋ ተመራማሪ አቶ ተክላይ ኃይሉ ናቸው፡፡

ለአካባቢው ተስማሚ የሆነ እናት የቀርከሀ ተክል በመትከል እየተካሄደ ያለው ምርምር ውጤት እየተገኘበት መሆኑንም ተናግረዋል ።

"የቀርቅሃ ተክል በአካባቢያችን ቢበቅልም ጥቅሙን ባለማወቃችን ያለ አግባብ ስናወድመው ቆይተናል" ያሉት ደግሞ በክልሉ ምዕራባዊ ዞን በወልቃይት ወረዳ የቆራሪት ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ አርሶ አደር ኃይሉ አስፋው ናቸው፡፡

በክልሉ ደቡባዊ ምስራቅ ዞን የደጉዓ ተምቤን ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ፎትየን አስፋው በበኩላቸው "ቀርካሃ በተለምዶ ለእንዝርትና ለሌሎች ትናንሽ የቤት ውስጥ መጠቀሚያዎች እንጂ ሌላ ከፍ ያለ ጥቅም ያለው አይመስለኝም ነብር ብለዋል" ፡፡

"አሁን ድረስ ቀርካሀን በመስኖ ለቲማቲም ማስደገፊያና ለደሮ ቆጥ መስሪያ ከማዋል ውጭ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን ሳላውቅ ቆይቺያለሁ" ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም