በኦሮሚያ ክልልና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መካከል ያለውን የአስተዳደር ጥያቄ መፍትሄ ይሰጣል የተባለ ኮሚቴ ተቋቋመ

123

አዲስ አበባ የካቲት 30/2011 በኦሮሚያ ክልልና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መካከል ያለውን የአስተዳደር ወሰን ጥያቄ  ዘላቂ መፍትሄ ይሰጣል ተብሎ የታመነበት ኮሚቴ ተቋቋመ።

ኮሚቴው የተቋቋመው በአስተዳደር ወሰን ጉዳዩ ዙሪያ ከዚህ በፊት የተደረጉ ጥናቶችን መሰረት በማድረግ እና ህዝቡን ያሳተፈ ዘላቂ መፍትሄ ማስቀመጥ ወሳኝ ሆኖ በመታመኑ እንደሆነ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኮሚቴው ከፌዴራል መንግስት፣ ከኦሮሚያ ክልል መንግስትና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ ስምንት አባላት አሉት።

በዚሁ መሰረት የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ኮሚቴውን በሰብሳቢነት ይመሩታል።

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ጠይባ ሀሰን፣ የኦሮሚያ ክልል በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪ አቶ አህመድ ቱሳ፣ የኦሮሚያ ክልል በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ የኮሚቴው አባል ናቸው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ እንዳወቅ አብጤ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔና የአዲስ አበባ ከተማ የከንቲባው የህዝብ አደረጃጀት አማካሪ አቶ ተስፋዬ ቤልጂጌ የኮሚቴው አባላት ናቸው።

የተዋቀረው ኮሚቴ በኦሮሚያ ክልልና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መካከል ያለውን የአስተዳደር ወሰን ጥያቄ ጉዳይ መፍትሄ የሚሆን ምክረ ሀሳብ እንዲያቀርብ አቅጣጫ እንደተቀመጠለትም በመረጃው ተመልክቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያስገነባቸውን 51 ሺህ 229 የ20/80 እና የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ በማውጣት ለእድለኞች የካቲት 27 ቀን 2011 ዓ.ም ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ይህንን ተከትሎ የኦሮሚያ ክልል መንግስት በማግስቱ ባወጣው መግለጫ  ''በአዲስ አበባና በኦሮሚያ መካከል ያለው የአስተዳደር የወሰን ጉዳይ እልባት ሳይሰጠው የጋራ መኖሪያ ቤቶች በእጣ ለባለ አድለኞች መተላለፋቸው ተገቢ አይደለም'' በማለት ተቃውሞውን መግለጹ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም