የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በስነ-ህንፃ ትምህርት ዘርፍ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ

87

ሶዶ የካቲት 30/2011 የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በስነ-ህንፃ ትምህርት ዘርፍ በመደበኛው መርሃ ግብር በመጀመሪያ ዲግሪ  ያሰለጠናቸውን 43 ተማሪዎችን ዛሬ አስመረቀ፡፡

በምረቃው ስነ-ስርዓት  የዩኒቨርስቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት  ዶክተር ወንድሙ ወልዴ እንዳሉት ተመራቂዎቹ በቆይታቸው የቀሰሙትን ዕውቀትና ክህሎት  በመጠቀም በሚሰማሩት ቦታ ህዝባቸውንና ሀገራቸውን በታማኝነት ማገልገል  ይገባቸዋል፡፡

በተለይም የሰለጠኑበት የሙያ ዘርፍ በሚፈቅደው ልክ አዳዲስ የፈጠራ ክህሎት በማከናወን በተግባር ላይ ማዋል እንደሚጠበቅባቸውም ገልፀዋል፡፡

ከተመራቂዎች መካከል እስከ አድማስ ግርማ በሰጠው አስተያየት ለአምስት ዓመት ተኩል በትምህርት ቆይታቸው የገጠማቸውን ፈተናዎች በትዕግስት በማለፍ ውጤታማ መሆናቸው እንዳስደሰተው ተናግሯል፡፡

በተለይም በዩኒቨርስቲው የስነ-ህንፃ ዘርፍ ለማዘመንና ብዛት ያላቸው ተማሪዎችን ለማሳተፍ የተሟላ የቤተ-ሙከራ፣ የልምምድ ዕቃዎችና የሰው ኃይል ሊሟላ እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡

ሌላው  ከፍተኛ ነጥብ በማምጣት የተሸለመችው በተልሄም ሰለሞን በበኩሏ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁማ ለውጤት መብቃቷን ገልጻለች፡፡

ተመራቂዋ እንዳለች በቀጣይም በሃገሪቱ በስነ-ህንጻ ዘርፍ ከዲዛይን አወጣጥ ጀምሮ እስከ ግንባታ የሚስተዋለውን ችግር ለማቃለል ያገኘችውን እውቀት በመጠቀም ውጤታማ ለመሆን የበኩሏን ጥረት ለማድረግ ተዘጋጅታለች፡፡

የተመራቂዋ የቤተልሔም አክስት ወይዘሮ መቅደስ በቀለ በሰጡት አስተያየት ከቤተሰብ የሚደረግ ድጋፍ ብቻ ሳይሆን በራሷ ጥንካሬ ጭምር ለላቀ ውጤት በመብቃቷ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ  ዛሬ ያስመረቃቸው ለሶስተኛ ጊዜ ሲሆን እስካሁንም ከ120 በላይ የዘርፉ ባለሙያዎችን አሰልጥኖ ማውጣቱ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም