ኤድስን ለመከላከል ተሳትፏቸውን እንደሚያጠናክሩ በነቀምቴ የዲስትሪክቱ ሰራተኞች ገለጹ

69

ነቀምቴ የካቲት 30/2011 የኤች.አይ.ቪ. ኤድስ ስርጭትን ለመከላከል ተሳትፏቸውን እንደሚያጠናክሩ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የነቀምቴ ዲስትሪክት ሠራተኞች ተናገሩ፡፡

የዓለም ኤድስ ቀን ምክንያት በማድረግ የዲስትሪክቱ 90 ሠራተኞች በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የደም ምርመራ በነቀምቴ አድርገዋል፡፡

ሠራተኞቹ በዚህ ወቅት  የበሽታው ስርጭት ለመግታት በየጊዜው በመመርመር ራሳቸውን በማወቅና ሌሎች የሕበረተሰቡን ክፍሎችም በሽታውን እንዲከላከሉ በማስተማር ለማገዝ  ወስነዋል ፡፡

በዲጋ ወረዳ የአርጆ ጉደቱ አገልግሎት መስጫ ጣቢያ ሠራተኛ  አቶ ተሾመ ወልደ ጊዮርጊስ በፍቃዳቸው የደም ምርመራ በማድረግ እራሳቸውን ማወቃቸውን በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡

የአካባቢም ሕብረተሰቡ በመመርመር ራሱን በማወቅ ከበሽታው ራሱን እንዲጠብቅ አስፈላጊውን ቅስቀሳ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡

ከኪረሙ ወረዳ የኪረሙ አገልግሎት መስጫ ጣቢያ ቴክኒሺያን ወጣት እንዳለ አራርሶ እንዳለው ተመርምሮ  እራሱን ማወቁ እንዳስደሰታውና በዚህም ተነሳስቶ ተሳትፎን በማጠናከር ሌሎችም በተመሳሳይ የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለመቀስቀስ ተዘጋጅቷል፡፡

የኦሮሚያ ክልል የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጫላ ቦንሳ ድርጅቱ ያሉት ብዛት ያላቸው ሠራተኞች ተምርምረው ራሳቸውን እንዲያውቁ ለማድረግ የቀኑ መከበር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኤች.አይ.ቪ.ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ በዳሶ በበኩላቸው  መስሪያ ቤታቸው የሰው ኃይሉን ከበሽታው ለመጠበቅ  በጀት በመመደብ እንደመደበኛው ስራው ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የድርጅቱ ሠራተኞች " ለኤች.አይ.ቪ.ይበልጥ ተጋላጭ ነን፣እንመርመር፣ራሳችንን እንወቅ " በሚል መሪ ሃሳብ የዓለም ኤድስ ቀን  በነቀምቴ አክብረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም