ደኢህዴን የክልሉ አመራሮች መድረክ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ

86

አዋሳ የካቲት 30/2011 ክልል አቀፉ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ/የደኢህዴን አመራሮች መድረክ መቋረጡ ህግን የጣሰ መሆኑን የክልሉ መንግስት ገለጸ፡፡

የተቋረጠው መድርክ በቀጣይ ቀናት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ደኢህዴን አስታውቋል፡፡

የክልሉ መንግስት ትላንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ለአራት ቀናት ይካሄዳል ተብሎ የታሰበው ክልል አቀፉ የአመራሮች መድረክ ተቋርጧል፡፡

መድረኩ የተቋረጠውም አንዳንድ አመራሮች ለውይይት የቀረበው ሰነድ የህዝብን ጥያቄ የሚፈታ አይደለም በሚል ባልተገባ መልኩ አቋርጠው በመውጣታቸው ነው።

የተደራጁ ቡድኖችም ተሰብሳቢዎች ባሉባቸው አዳራሾች በመግባት ተወያዮቹ ውይይቱን አቋርጠው እንዲወጡ አድርገዋል፡፡

ድርጊቱ ህግን የጣሰ ነው ያለው የክልሉ መንግስት መግለጫ በውይይቱ መቋረጥ መጉላላት ለገጠማቸው የክልሉ አመራሮች ይቅርታ የጠየቀ ሲሆን የሃዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ላሳዩት ጨዋነት አመስግኗል፡፡

የሃዋሳ ከተማና አካባቢዋ የሃገር ሽማግሌዎች የሃይማኖት መሪዎችና ወጣቶች የክልሉ መንግስት የጀመረውን የለውጥ ሂደት እንዲያግዙ ጥሪ አቅርቧል፡፡

በተፈጠረው መስተጓጎልም በሰውና በንብረት ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አለመድረሱን ጠቅሶ የክልሉ መንግስት የክልሉን ሰላም የመጠበቅ ሃላፊነቱን እንደሚወጣ አስታውቋል፡፡

ክልሉን የሚመራው የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ደኢህዴን በበኩሉ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው ክልል አቀፉ የአመራሮች መድረክ በሚቀጥሉት ቀናት ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው።

"በውይይቱ የሚቀመጡ አቅጣጫዎች የክልሉን ህዝቦች ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው ያለው" መግለጫው መድረኩ እንዲቋረጥ ያደረጉ አካላት በህግ እንደሚጠየቁም ገልጿል።

"በ10ኛው የደኢህዴን ጉባኤ የተቀመጡ አቅጣጫዎችን የደርጅቱ ስራ አስፈጻሚና ማዕካለዊ ኮሚቴ በቅርቡ መገምገሙን ተከትሎ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር የተጀመረው ውይይት እንዳይሳካ የተደራጁ አካላት መስተጎጓጎል ፈጥረዋል" ብለዋል፡፡

በዚህም በአንዳንድ አመራሮች ላይ መንገላታት ደርሷል ያለው ጽህፈት ቤቱ ተሰብሳቢ አመራሮች ላሳዩት ትዕግስትና ጨዋነት አመስግኖ ለተፈጠረው መጉላላትም ይቅርታ ጠይቋል፡፡

የሲዳማ ህዝብ ከሌሎች የክልሉ ነዋሪዎች ጋር አብሮ የመኖር ትልቅ ባህል ያለው እንግዳ ተቀባይ በመሆኑ ድርጊቱ አንዳንድ የተደራጁ ቡድኖች  የፈጸሙት እንጂ ብሄሩን የሚወክል እንዳልሆነም አስታውቋል።

ማንኛውም ጥያቄ በተደራጀና በዴሞክራሲያዊ መንገድ መቅረብ እንዳለበት የጠቆመው መግለጫው ህገ-መንግስታዊው የዜጎች የመሰብሰብና በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት ሊከበር እንደሚገባም አመልክቷል።

በሃዋሳና አካባቢው ያሉ የሃገር ሽማግሌዎች የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ችግሩ እንዳይባባስ ላደረጉት ጨዋነትም ምስጋናውን አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም