የ10ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የመጀመሪያ ቀን ውሎ ያለምንም ችግር መጠናቀቁ ተገለጸ

100
ግንቦት 22/2010 የ10ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የመጀመሪያ ቀን ውሎ ያለ ምንም ችግር መጠናቀቁን የሀገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ አስታወቀ። የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዘሪሁን ዱሬሳ በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት፥ በዛሬው እለት የ10ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ባሉ የፈተና ጣቢያዎች የተጀመረ ሲሆን በዛሬው ውሎውም ሶስት የትምህርት ዓይነቶች ፈተና ተሰጥቷል። በጧት ፈረቃ አማርኛና እንግሊዝኛ ከሰዓት ደግሞ የሂሳብ ትምህርት ፈተና ነው በዛሬው እለት የተሰጠው። በአዲስ አበባ ተዘዋውረን ባደረግነው ቅኝት ተማሪዎቹ በተረጋጋ ሁኔታ ፈተናቸውን ሲፈተኑ ውለዋል። በቅኝታችንም ያነጋገርናቸው የፈተና ጣቢያ ሃላፊዎችና ተማሪዎችም የብሄራዊ ፈተናው የመጀመሪያ ቀን እንደመሆኑ ምንም የጎላ ችግር ሳይከሰት መጠናቀቁን ነው የገለፁልን። ተማሪ ፋንታሁን የበላይ ዘለቀ ቁጥር 1 ሁለተኛ ደረጃ የ10ኛ ክፍል የልዩ ፍላጎት ተማሪ ሲሆን፥ ለሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና በቂ ዝግጅት አድርጎ ፈተናው በጀመረበት ዕለት መገኘቱን ገልጿል። ተማሪ ፋንታሁን እንደሱ ዓይነ ስውራን የሆኑ ተማሪዎች የፈተና ጥያቄዎችን በአግባቡ ማንበብ የሚችሉ ብቁ መምህራን ተመድቦላቸው እየተፈተኑ መሆኑን አንስቷል። ከናዝሬት ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል የብሄራዊ ተፈታኝ ተማሪ ማርታ በዳግማዊ ምኒልክ መሰናዶ የፈተና ጣቢያ ከሚፈተኑ 1 ሺህ 85 ተማሪዎች አንዷ ናት። ተማሪዋ እንዳለችው በፈተናው የመጀመሪያ ዕለት የፈተና መግቢያ መታወቂያ ረስታ ብትመጣም ፈታኞቹና የጣቢያው ሃላፊዎች ተነጋግረውና በፎቶግራፍ አረጋግጠው እንድትፈተን አድርገዋታል። ሆኖም ፈተና ከተጀመረበት 20 ደቂቃ ዘግይታ መምጣቷ መጨናቀቅ እንደፈጠረባት ያነሳችው ተማሪ ማርታ፥ ከዛሬው ስህተቷ መማሯንና በቀጣይ ቀናትም ሌሎችም ሳያረፍዱ መታወቂያቸውን ይዘው በጣቢያ በመገኘት ፈተናቸውን እንዲፈተኑ መክራለች። በዳግማዊ ምኒለክ መሰናዶ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ጣቢያ ሃላፊ የሆኑት ካሳሁን መርጋ፥ ከሰባት ትምህርት ቤት የተውጣጡ 1 ሺህ 85 ተማሪዎች ከዛሬ ጀምሮ ፈተና እየወሰዱ መሆኑን ገልፀዋል። በፈተናው የመጀመሪያ ቀን አንድ ተፈታኝ ፈተናው ከተጀመረ 50 ደቂቃ አርፍዶ በመድረሱ የአማርኛ ፈተና ሳይፈተን ከመቅረቱ ውጭ ሌላ ችግር ሳያጋጥም መጠናቀቁን ነው አቶ ካሳሁን የተናገሩት። ዶክተር ዘሪሁን በበኩላቸው የዘንድሮው ፈተና ከዚህ በፊት ካሉት በተሻለ መልኩ በተረጋጋና በሰላማዊ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ነው ያነሱት። ተማሪዎች በራሳቸው በመተማመን ተረጋግተው እየተፈተኑ እንደሚገኙና በዛሬው የፈተና ውሎ ኩረጃ እንዳይኖርና መረባበሽ እንዳይፈጠር ከወላጆች፣ ከፀጥታ አካላትና ከመምህራን የተውጣጡ ኮሚቴዎችን በማቋቋም እየተሰራ ነው ብለዋል። ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፥ በቀጣዮቹ ቀናትም ፈተናው በሰላም እንዲጠናቀቅ የተቀናጀ የቁጥጥርና የክትትል ስራው እንደሚቀጥል ገልፀዋል። በሀገሪቱ ያለው መረጋጋት ለዘንድሮው ፈተና አዎንታዊ  አስተዋፅአ እንዳለው ነው ያነሱት። ለተማሪዎች፣ ለፈታኝ መምህራንና ሱፐርቫይዘሮችም በቂ ማብራሪያ መሰጠቱን ጠቅሰው ወላጆችም የተሻለ ግንዛቤ መያዛቸው ተማሪዎችን በመምከር በፈተና ሂደቱ ላይ የራሳቸውን አዎንታዊ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ጠቁመዋል። ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎችን  በትራንስፖርትም ሆነ በሌሎች አገልግሎቶች ቅድሚያ በመስጠት እንዲተባበር መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። በበላይ ዘለቀ፣ በየካቲት 12፣ በዳግማዊ ምኒልክና ሌሎችም የመዲናዋ ትምህርት ቤቶች ተዘዋውረን ያነጋገርናቸው የፈተና ጣቢያ ሃላፊዎችና ተማሪዎች የመጀመሪያው ቀን ፈተና በሰላም መጠናቀቁን ጠቅሰዋል። የ10ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ከዛሬ ጀምሮ እስከ መጪው አርብ ለተካታታይ ሶስት ቀናት እየተሰጠ ሲሆን፥ በመላው ሀገሪቱ ከ1 ነጥብ 2  ሚሊየን በላይ ተማሪዎች በ2 ሺህ 709 ጣቢያዎች እየተፈተኑ ነው። ከተፈታኞቹ ውስጥ 45 በመቶዎቹ ሴቶች መሆናቸውን ኤጀንሲው ገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም