የቴሌኮሚኒኬሽንና የፖስታ አገልግሎት የቁጥጥር ሥርዓትን ለመዘርጋት የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

705

አዲስ አበባ የካቲት 29/2011 የቴሌኮሚኒኬሽንና የፖስታ አገልግሎት የቁጥጥር (ሬጉሌሽን) ሥርዓትን ለመዘርጋት የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።

‘የኮሚኒኬሽን አገልግሎት ረቂቅ አዋጅ’ በሚል የተዘጋጀው ህግ የኮሚኒኬሽን ዘርፉን ለመምራትና ለመቆጣጠር እንደሚያስችል ሚኒስቴር ዴኤታው ዶክተር እዮብ ተካልኝ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ገልፀዋል።

በመንግሥት ይዞታ ሥር የሚገኙ የልማት ድርጅቶችን ለግሉ ዘርፍ  የማስተላለፍ ተግባር ለገንዘበ ሚኒስቴር መሰጠቱንም አክለዋል።

በዚህም መሰረት የቴሌኮሚኒኬሽንና በፖስታ አገልግሎት የሬጉሌሽን ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን ነው ሚኒስቴር ዲኤታው ያመለከቱት።

ረቂቅ አዋጁ የተዘጋጀው ለዘርፉ ከተቋቋመው የቴክኒክ ኮሚቴና የአማካሪ ቡድን ጋር በመተባበር ነው።

ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የውጭ የዘርፉ ባለሙያዎችም አዋጁን እንደተመለከቱት ገልጸው ከሌሎች አገራትም ልምድ ተቀምሯል ነው ያሉት። 

ረቂቅ አዋጁ በአገሪቱ ከኮሙኒኬሽን ዘርፍ ጋር በተያያዘ የዲጂታል ገበያ ለመገንባት፣ ኢንቨስትመንት ለማስፋፋት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ብለዋል።

ለኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሰጪዎች ፈቃድ የሚሰጥና ዘርፉን የሚመራ፣ የሚቆጣጠር፣ ነጻና ገለልተኛ ሬጉላቶሪ ባለሥልጣን ለማቋቋም እንደሚረዳ ገልጸዋል።

የሬዲዮ ፍሪኪዌንሲ ስፔክትረም በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውልና ተገቢውን ክፍያ ለመሰብሰብ እንዲሁም የኮሚኒኬሽን ዘርፉን ለማስፋት እንደሚጠቅም ተናግረዋል።

በኢንዱስትሪው የሚከሰቱ አለመግባባቶችን የሚዳኝ የይግባኝ ሰሚ አካል ለማቋቋም እንደሚረዳም ጠቅሰዋል።

ረቂቅ አዋጁም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውይይት ተደርጎበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲያጸድቀው የውሳኔ ኃሳብ መሰጠቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የኢትዮ-ቴሌኮምን ጨምሮ የተለያዩ ግዙፍ የአገሪቱ ኩባንያዎችን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ወደግል ለማዘዋወር የሚያስችል ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።