በሴቶች የተመራው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ልኡካን ቡድን ኦስሎ ገባ

73

አዲስ አበባ የካቲት 29/2011 ሙሉ በሙሉ በሴቶች የተመራው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የልዑካን ቡድን ኖርዌይ ኦስሎ ሲደርስ ደማቅ አቀባበል ተደረገለት።

ዓለምአቀፉ የሴቶች ቀንን በማስመልከት በዋና አብራሪ አምሳለ ጓሉ የተመራው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ትናንት ምሽት ከአዲስ አበባ በመነሳት ዛሬ ጠዋት ኦስሎ ገብቷል።

የአውሮፕላኑ አብራሪ፣ ረዳት አብራሪ፣ የበረራ አስተናጋጆችና ቴክኒሽያኖች ሴቶች ናቸው።

የአየር ትራፊክ ቁጥጥር ፣ የጭነት ቁጥጥር ፣ የበረራ  መለኪያ ፣ የበረራ ደህነነት ቁጥጥር ከትኬት ቢሮ ጀምሮ እስከ አውሮፕላኑ መነሻ ድረስ ሙሉ በሙሉ በሴቶች የተመራ ነው።

የአየር መንገዱ የገበያ አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት እና በኢትዮጵያ የኖርዌይ አምባሳደር በበረራው ታድመዋል።

በሴቶች የተመራው ይህ ታሪካዊ  የበረራ ልዑካን ቡድን በስቶኮልም ስውዲን እንዲሁም ኦስሎ ኖርዌይ ሲደርስ በኢትዮጵያ ኮሚኒቲና በኢትዮጵያ ኤምባሲ ሰራተኞች ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።

በረራው ኢትዮጵያውያን ሴቶች አይደፈሩም የተባሉ ስራዎችን በመስራት ከአገራቸው አልፎ ለዓለም ህዝቦች ብቃታቸውን ያሳዩበት መሆኑም ነው በዚሁ ጊዜ የተነገረው።

አየር መንገዱ በየዓመቱ የሚከበረውን የሴቶች ቀን በዓል አስቦ ከመዋል ባለፈ የሴቶችን እኩልነት ለማረጋገጥና በተግባር ለማሳየት ሴቶችን ወደ ፊት ለማምጣት እየሰራ መሆኑን የአየር መንገዱ የገበያ አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ራሄል አሰፋ ገልጸዋል።

አየር መንገዱ በሴቶች ብቻ የተመራ በረራ ሲያርግ ይህ ለ5ኛ ጊዜ ሲሆን ቀደም ሲል ባንኮክና በቦነሳይረስ ተመሳሳይ ጉዞ ማድረጉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም