በነቀምትና አምቦ ከተሞች ለህዝብና ቤት ቆጠራ አስፈጻሚዎች ስልጠና እየተሰጠ ነው

63

ነቀምት ካቲት 29/2011 ለአራተኛው ዙር የህዝብና ቤት ቆጠራ አስፈጻሚዎች የተዘጋጀ የአሰልጣኞች ስልጠና  በነቀምትና በአምቦ ከተማ እየተሰጠ ነው።

በነቀምቴ ከተማ በተጀመረው ስልጠና ላይ ከከተማው አስተዳደር፣  ከቄለም፣ ሆሮጉድሩ፣ ምስራቅና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች የተውጣጡ 550 ሰልጣኞች እየተሳተፉ ነው።

በማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የነቀምቴ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ በላይ አቦማ እንደገለፁት ስልጠናው እስከ መጋቢት 8 ቀን 2011 ዓ.ም ይቆያል ።

ተሳታፊዎች  ወደ መጡበት አካባቢ ሲመለሱ ለሱፐርቫይዘሮችና ለህዝብና ቤት ቆጠራ ባለሙያዎች ስልጠና እንደሚሰጡ አመላክተዋል ።

የምሥራቅ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ በቀለ በበኩላቸው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ በሀገሪቱ  ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች ፋይዳው ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በአምቦ ከተማም እየተሰጠ ባለው ተመሳሳይ ስልጠና 595 አስፈጻሚዎች እየተሳተፉ ነው ።

የስልጠናው ተሳታፊዎች ከምእራብ፣ ደቡብ ምዕራብና ሰሜን ሸዋ ዞኖች ናቸው ።

የምዕራብ ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ግርማ አጋማ  በህዝብ ቆጠራው የሚሳተፉ አካላት በስነ-ምግባርና በኃላፊነት መንፈስ ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በሀገር ደረጃ ለሚካሄደው ቆጠራ 152 ሺህ ቆጣሪዎችና 37 ሺህ ተቆጣጣሪዎች ስልጠና ተሰጥቷቸው የተግባር ፈተና ከወሰዱ በኋላ ወደ ቆጠራው ይገባል፡፡

ቆጣሪዎችን የሚያሰለጥኑ 8 ሺህ ባለሙያዎች በመላ ሀገሪቱ ስልጠና እየተሰጣቸው መሆኑም ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም