በሰሜን ወሎ ዞን የበልግ ዝናብን በመጠቀም ከ13 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፈነ

76

ወልዲያ የካቲት 29/2011 በሰሜን ወሎ ዞን  ወቅቱን ጠብቆ እየጣለ ያለውን የበልግ ዝናብ በመጠቀም ከ13 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ሞገስ አለሜ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በተያዘው  የበልግ ወቅት 32 ሺህ 700 ሄክታር መሬት  ለማልማት እየተሰራ ነው፡፡

ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተካሄደ የእርሻ ስራ እንቅስቃሴም መሬቱን በዘር ተሸፍኗል፡፡

የበልግ እርሻ ሥራው  እየተከናወነ ያለው በዋድላ፣ ጋዞ ፣ አንጎትና ግዳን፣ ላስታ፣ ራያ ቆቦ፣ ሀብሩና ጉባ ላፍቶ ወረዳዎች ነው።

በበልግ ዝናብ  ከሚለማው መሬትም ከ450 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጹት ባለሙያው፣ ከ57 ሺህ በላይ  አርሶ አደሮች በሥራው መሳተፋቸውን አስረድተዋል።

የዘንድሮ የበልግ ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ መጣል በመጀመሩ ዕቅዱ ይሳካል ተብሎ አንደሚጠበቅ ጠቅሰዋል፡፡

የበልግ እርሻውን ውጤታማ ለማድረግ ማዳበሪያ መሰራጨቱን ባለሙያው ተናግረዋል።

በጉባ ላፍቶ ወረዳ የቀበሌ 13 ነዋሪ አርሶ አደር ጫኔ እውኔ የዘነድሮው የበልግ ዝናብ ቀድሞ መግባቱ ለእርሻ ስራቸው  ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው አስረድተዋል።

ቀደም ብለው ዝግጅታቸውን በማጠናቀቃቸው ባለፈው ሳምንት በፊት ማሳቸውን በዘር መሸፈናቸውን  ጠቁመዋል።

የጋዞ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ደምሌ ተስፋው በበኩላቸው "የዘንድሮ የበልግ ዝናብ ከሚጠበቀው ጊዜ ቀድሞ በመምጣቱ ለእርሻ ስራው ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል" ብለዋል።

ባለፈው ዓመት የበልግ ዝናብ ዘግይቶ በመምጣቱ በዘርፉ የተከናወነው ስራ በቂ እንዳልነበር ከዞኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም