የፍትህ አካላት ለሕግና ፍትህ ልዕልና መትጋት እንዳለባቸው ኢንስትትዩቱ አሳሰበ

78

አዳማ የካቲት 29/2011 የፍትህ አካላት በለውጥ ለሕግና ፍትህ ልዕልና መትጋት እንዳለባቸው የፍትህና ሕግ ምርምርና ስልጠና ኢንስቲትዩት አሳሰበ።

ኢንስቲትዩቱ ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት ለፌዴራልና ክልሎች የፍትህ ዘርፍ መካከለኛ አመራሮች ለሶስት ቀናት ያዘጋጀው የአሰልጣኞች ስልጠና መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።

የኢንስቲትዩቱ የስልጠና ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን አበበ በዚህ ወቅት እንዳስታወቁት የሕግ የበላይነትና ፍትሃዊነት በሌለበት በሁሉም መስክ የህዝቡን ተሳትፎ ማረጋገጥ ያዳግታል።

በመሆኑም በየደረጃው የሚገኙ የፍትህ አካላት በለውጥ ምህዋር ውስጥ በመግባት በሕግ ሥርዓቱ ላይ ያሉ ክፍተቶችን በማሻሻል የሕዝብን እምነትና ከበሬታ መልሰው ለማግኘት እንዲተጉ አስገንዝበዋል።

ባለፉት ዓመታት የፍትህ ሥርዓቱ ያሉበትን ችግሮች ለማቃለል ማሻሻያ ጥረት ቢደረግም፤ የአመራሩና የፈጻሚውን ድርሻ በአግባቡ ባለመከናወኑ ውጤት ማምጣት  አልተቻለም ብለዋል።

በዚህም ምክንያት ዜጎች በፍትህ አገልግሎት ላይ ከቅሬታ በላይ ተቃውሞአቸውን በአደባባይ መግለፃቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የሕዝቡን አመኔታና ክብር መልሶ ለማግኘት መሥራት እንዳለባቸው አቶ መስፍን አሳስበዋል።

እያደገ ያለው ምጣኔ ሀብት የሚሸከም የፍትህ ሥርዓት መገንባት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

ይህን እውን ለማድረግ የፍትህ ዘርፍ አገልግሎት በቀላሉ ዋጋ ሊተመንለት አይችልም ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ሙያዊ ብቃት፣ሕዝባዊ ወገንተኝነት፣ታማኝነት፣ጥብቅ ሥነ ምግባር፣እውነተኝነትና ሙያዊ ፍቅርን ይጠይቃል ብለዋል።

እንደ አቶ መስፍን ገለፃ በፍትህ ሥርዓቱ ላይ ያሉ ጉድለቶችን ለመፍታት የአቅም ግንባታ ስልጠናን ጨምሮ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው እየተተገበሩ ሲሆን፣መድረኩ የዚሁ እንቅስቃሴ አካል ነው።

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ በዛብህ ገብረየስ በበኩላቸው ስልጠናው በአገሪቱ የተጀመረው ለውጥ ግለቱን ጠብቆ እንዲቀጥል በውጤታማነትና ቀልጣፋ አገልግሎት አሰጣጥ የዜጎችን እርካታ የማሻሻል ዓላማ እንዳለው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም