ሚኒስቴሩ በልዩ ሁኔታ የግብዓት አቅርቦት ለሚያስፈልጋቸው ተቋማት ፈጣን ምላሽ መስጠት ይገባዋል-የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

1819

አዲስ አበባ ግንቦት22/2010 ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በስሩ ለሚገኙ ተጠሪ ተቋማት ግብዓት በአፋጣኝ ማሟላት እንደሚገባው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

የምክር ቤቱ የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ቀደም ሲል በጳውሎስ ሆስፒታል፣ በመድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ፣ በህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ በምግብ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን እንዲሁም በጉለሌው የሰላም ጤና ጣቢያ  ላደረገው የመስክ ምልከታ  ግብረ መልስ ሰጥቷል።

በተጨማሪም ቋሚ ኮሚቴው የሚኒስቴሩን የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አድምጧል።

የቋሚ ኮሚቴው አባል ወይዘሮ ሰሚራ ሱልጣን በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ሚኒስቴሩ በስሩ ላሉ ተጠሪ ተቋማት ከተቋቋሙበት ዓላማና የስራ ባህሪ አኳያ እየሰጡ ላሉት አገልግሎት የሚያደርገው ድጋፍ በሚፈለገው ልክ አለመሆኑን በምልከታው አረጋግጠዋል።

ለአብነትም ለኩላሊት ንቅለ ተከላ ማዕከል የመድሃኒትና የህክምና መሳሪያ አቅርቦት፣ በህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለጥናትና ምርምር የሚውል የኬሚካልና ሪኤጀንት አቅርቦት፣ ለመድሃኒት ፈንድ አቅርቦት ኤጀንሲና ለምግብ መድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደር ባለስልጣን የሚያደርገው ድጋፍና ክትትል ዝቅተኛ ነው።

ይህ ደግሞ በነፍስ ወከፍ የህክምና አገልግሎት ማግኘት ላለባቸው ዜጎች እንቅፋት እየሆነ ነው ይላሉ።

ሌላው በህክምና ተቋማት የሚስተዋለውን የውሃ አቅርቦት ችግርንም ለመቅረፍ ሚኒስቴሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የሚያደርገው ጥረትም በቂ አለመሆኑን ነው ወይዘሮ ሰሚራ የጠቆሙት።

ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን በበኩላቸው በተቋማቱ ያሉ የግብዓት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ከፋይናንስና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የግዢ ሂደቱን ለመፈጸም ፍቃድ ተጠይቋል ብለዋል።

በዚህም የሪኤጀንት ግዥ ለመፈጸም ከአምስት የሬኤጀንት አቅራቢ ተቋማት ጋር የሶስት ዓመት ስምምነት መፈራረማቸውን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ በልዩ ሁኔታ ግብዓት ለሚያስፈልጋቸው ተቋማት ብቻ ሳይሆን በሚኒስቴሩ ስር ላሉ ሆስፒታሎችም በቀላሉ መሳሪያዎቹን የሚገዙበት አሰራር የሚፈጠር በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት ያስችላል ነው ያሉት።

በተጨማሪም አነስተኛ የህክምና መሳሪያ ግዥ ለሚያስፈልጋቸው ተቋማትም እንዲሁ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ‘ዩኖስ’ የሚባል የህክምና መሳሪያ ግዥ የሚፈጽም ተቋም ፍቃድ እየተጠየቀ ነው፤ በቅርቡ ለማሟላት ጥረት ይደረጋልም ብለዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም የመድሃኒት አገዛዝ አሰራሩና የህክምና መሳሪያ ግዥ ፖሊሲው በአዲስ መልክ እንዲቀየር ሚኒስቴሩ ጥናት እያካሄደ ነው፤ አዲስ የሚጠናው ጥናትም የግዥ ሂደቱ ላይ ያለውን መጓተት ያስቀራል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በጤና ተቋማት ያለው የህክምና መስጫ ክፍሎች ጥበትና የአንቡላንሰ እጥረት፣ ህጋዊ የባህል ህክምናን ከዘማናዊ ጋር ለማጣጣም የሙያተኞች ቅንጅታዊ አሰራር ክፍተት፣ የህክምና ተቋማት የቦርድ ውይይቶች ችግር ፈቺ እንዲሆኑ እየተከናወኑ ስላሉ ተግባራት፣ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው  መድሃኒቶች አወጋገድና የከተማ ጤና ኤክስቴንሽን መቀዛቀዝን በሚመለከት ጥያቄ አንስተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ከበደ ወርቁ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሙን በአዲስ መልክ ለማጠናከር የዳሰሳ ጥናት በመካሄዱ የጤና ኤክስቴንሽን ማሻሻያ ፕሮግራምና የከተማ ጤና ፕሮግራሞች ተቀርጿል ብለዋል።

የማስፋፊያ ቦታዎችንና የአንቡላንስ ጥያቄዎችን ለመፍታትም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰሩ እንደሆነ አክለዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ አበባ ዮሴፍ እንደገለጹት በህክምና ተቋማት የመረጃ ልውውጡ በኤሌክትሮኒክስ የተደገፈ በመሆኑ የታካሚዎችን እንግልት መቀነሱን፣ የእናቶችና የህጻናት ጤና አጠባበቅ፣ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን አባላት ቁጥር ማብዛት ቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ ተመልክቶታል ብለዋል።

የህክምና ተቋማት የማስፋፊያ ጥያቄዎች፣ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው መድሃኒቶች ክምችት፣ የመድሃኒት ማስቀመጫ መጋዘኖች ጥራት መጉደል፣ በህክምና ተቋማት የተጀመሩና ረጅም ጊዜ የፈጁ ግንባታዎች እንዲሁም ህጋዊ የባህል ህክምና ማጠናከሩ ትኩረት የሚሹ እንደሆኑ ገልጸዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ ከ16 ሺህ በላይ የጤና ኬላዎች፣ ከ3 ሺህ 700 በላይ ጤና ጣቢያዎችና ከ411 በላይ ሆስፒታሎች አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው።