በባህር ዳር ከተማ ሌሊት የተነሳ የእሳት ቃጠሎ ከፍተኛ ጉዳት አደረሰ

80

ባህርዳር የካቲት 29/2011 በባህር ዳር ከተማ ቀበሌ 05 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ዛሬ ሌሊት በተነሳ የእሳት አደጋ ለጊዜው ግምቱ ያልታወቀ ንብረት መውደሙን የከተማው አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው ሃላፊ ኮማንደር ዋለልኝ ዳኘው ለኢዜአ እንደገለፁት አደጋው የደረሰው ከለሊቱ 8፡00 ሰዓት አካበቢ ጀምሮ ነው።

በደረሰው አደጋም ለጊዜው ቁጥራቸው ያልታወቀ፣ የመኖሪያ ቤቶች፣ የወርቅና ብዕር መሸጫ ሱቆች፣ ሆቴሎችና መሰል አገልግሎት የሚሰጡ ቤቶች ተቃጥለዋል፡፡

“አደጋው በሰው ህይወት ላይ ያደረሰው ጉዳት የለም” ያሉት ኮማንደሩ ለጊዜው ግምቱ ያልታወቀ ከፍተኛ ንብረት መውደሙንም ገልፀዋል፡፡

የአደጋው መንስኤ እስከ አሁን እንዳልታወቀና የማጣራት ስራ ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

“ቃጣሎውን የእሳት አደጋ መከላከያ መኪናዎችና የከተማው ህዝብ ባደረገው ጠንካራ ርብርብ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይዛመት አድርጎታል” ብለዋል፡፡

በአደጋው ለጉዳት የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን ጊዜያዊ መጠለያ ለመስጠት የከተማው ህዝብ ድንኳን የመጣል እንቅስቃሴ እንደጀመረም ተመልክተናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም