ከዕድሜ ክልላቸው ውጪ የሚወዳደሩ አትሌቶች ታዳጊዎችን እንዳይደፍቁ መፍትሄ ያስፈልጋል

72
ይሁኔ ይስማው (ኢዜአ)    የ10ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና ላይ ለመቀመጥ አንድ ሳምንት እየቀረው ወደ አሰላ ያቀናው የ17 ዓመቱ ታዳጊ ባንተጊዜ እንዳሻው በአትሌቲክስ ስፖርት ወደፊት ትልቅ ደረጃ የመድረስ ራዕይ ሰንቋል። በ800 ሜትር ርቀት ጥሩ ብቃት እንዳለው የሚያምነውና ወደፊት በዓለም መድረክ የመታየት ህልም ያለው ይህ ታዳጊ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን አሰላ ከተማ ከግንቦት 15 ቀን 2010 ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በተካሄደው የኢትዮጵያ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለመካፈል የድሬዳዋ አስተዳደርን ወክሎ ተገኝቷል። ባንተጊዜ በአትሌቲክስ ስፖርት ጥሩ ብቃት ያለው በመሆኑ የወደፊት እንጀራው አትሌቲክስ እንደሆነ በማመን ዘወትር ይተጋል። ከትምህርቱ ጎን ለጎን የአትሌቲክስ ስፖርት ስልጠና ይከታተላል።እንደ ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች እሱም የሀገሩን ስምና ዝና ለማስጠራት ይጓጓል ይናፍቃል። እሱን የመሰሉ በአትሌቲክስ ስፖርት ጎልተው ለመውጣት የሚለፉና የሚደክሙ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች አሉ። ድካማቸው ፍሬ አፍርቶ በዓለም የአትሌቲክስ ስፖርት መድረክ ገነው በመውጣት ራሳቸውንና አገራቸውን ያስጠሩ አሉ። አሰላ በተካሄደው ሻምፒዮና ላይ የተሻለ ውጤት ይዘው ለመውጣት ህልም የነበራቸው ባንተጊዜን የመሳሰሉ ወጣቶች በዕድሜ ተገቢነት ምክንያት የሃሳባቸውን ሳይሞሉ የቀሩበት ሁኔታ በውድድሩ ላይ መታዘብ ችለናል። ባንተጊዜ እንደሚለው 'ለበርካታ ዓመታት በስፖርቱ ውስጥ ሲወዳደሩ የነበሩ ተወዳዳሪዎች የዕድሜ ገደባቸው ከሚፈቅድላቸው ውጪ በመሳተፍ የነገ ተስፈኛ ታዳጊዎችን ህልም አጨናግፈዋል'። በአሰላ አስተናጋጅነት የተካሄደው ስድስተኛው የኢትዮጵያ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከ20 ዓመት በታች ያሉ ተተኪ ስፖርተኞች የሚካፈሉበት ውድድር ነበር። “እኔ በምወዳደርበት የ800 ሜትር ርቀት ስማችን እየተጠራ ወደ መሮጫ መም ስንገባ ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች ነው ተብሎ ወደ ሜዳ የገቡት አብዛኛዎቹ አትሌቶች ለብዙ ዓመታት የተወዳደሩ ነባር አትሌቶች መሆናቸውን ስመለከት ግን ገና ከውድድሩ በፊት ተስፋ የሚያስቆርጡ ሁኔታዎች ነበሩ» ይላል ታዳጊው። ይህ የባንተጊዜ ስጋት የሌሎችም ትክክለኛ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሌሎች የውድድሩ ተካፋዮች ስጋት እንደሆነ የኢዜአ ሪፖርተር ትዝብት ነው። ከ20 ዓመት በታች በሚለው የውድድር ክልል ውስጥ ዕድሜያቸው ከገደቡ ዘሎ ወደ 30ዎቹ የሚጠጉ አትሌሎቶች በሻምፒዮናው ለመፎካከር መቅረባቸውን መታዘብ ይቻላል። አንዳንዶቹ ተወዳዳሪዎች በትክክለኛ የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ታዳጊ አትሌቶች ጋር ሲነጻጸሩ ሚዛኑን የሳተ የፉክክር መንፈስ የሚፈጥር ይሆናል። በዚህ በልምድም በዕድሜም ተመጣጣኝነት በጎለው ውድድር ውስጥ የሚገቡ ጠንካራ የሆኑ ታዳጊ አትሌቶች ያለአቻ የሆነ ፉክክር ውስጥ በመግባት የተሻለ ውጤት ያለማምጣት ተስፋ አስቆራጭ ስሜት ውስጥ የሚከታቸው ይሆናል። አሰላ ላይ በታየው ያለአቻ የሆነ ውድድር ውስጥ ገብቶ የነበረው ታዳጊ አትሌት ባንተጊዜ በተወዳደረበት የ800 ሜትር ሩጫ 6ኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቁ ገና በማጣሪያው ሊሰናበት ችሏል። በዚህ መልኩ በአሳዛኝ ሁኔታ ከውድድር ውጭ የሆነው ባንተጊዜ 'ካለእድሜአቸው ገብተው የማይገባቸው ውጤት ለማገኘት የሚፈለጉ አትሌቶች ተጨማሪ ሀይልን የሚሰጥ አበረታች ንጥረ ነገር እንደሚስዱ አትሌቶች አይነት ድርጊት በመሆኑ ሊቆም ይገባል' ሲል ተናገሯል። በውድድሩ ላይ ተገኝተን እንደታዘብነው ከሆነና ከተወደዳሪዎቹ ባገኘነው መረጃ መሰረት በዚህ ሻምፒዮና ከተሳተፉት ከ1ሺህ በላይ ተወዳዳሪ ስፖርተኞች መካከል በተቀመጠው የእድሜ ደረጃ የገቡት ጥቂቶች ናቸው። ብዙዎቹን ተወዳዳሪዎች በተመለከተ የስፖርት ቤተሰብ የዚህ ውድድር መጠሪያ የሆነውን 'የወጣቶች ሻምፒዮና' ጥያቄ ውስጥ ይከታል። እድሜአቸውን መሰረት አድርገው የሚመጡ አትሌቶች በቀላሉ ስለሚሸነፉ ተስፋ የሚያስቆር እየሆነባቸው ነው። በትክክለኛ የዕድሜ ወሰናቸው የሚወዳደሩትን የነገ ተስፋ ያላቸው ስፖርተኞች ተስፋ ላለማክሰም ተገቢው ክትትል ሊደረግ ይገባል። በተለይ ወቅታዊ የሆነ ውጤት ለማግኘት ሲሉ ተገቢነት የሌላቸውን ተወዳዳሪዎች ይዘው የሚቀርቡ አሰልጣኞችና የቡድን መሪዎች ከድርጊታቸው በመቆጠብ ለአገር ስፖርት እድገት መስራት ይጠበቅባቸዋል። ችግሩ በአሁኑ የኢትዮጵያ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ብቻ የተከሰተ ሳይሆን በተደጋጋሚ የሚታየ ችግር ነው። ይሁን እንጂ እስከሁን መፈታት ያልቻለ ችግር ሆኖ ቀጥሏል። በዚህ ምክንያት ከእድሜቸው በላይ የሆኑ ልጆች የሌሎችን እድል በመዝጋት የክልልና የክለብ ሀላፊዎችና አሰልጣኞች ጊዜያዊ ውጤት ለማግኘት መንቀሳቀስ በረጅም ጊዜ ውስጥ የሚያስከትለው ጉዳት እንዳለ መገንዘብ ያስፈልጋል። በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የስፖርት ባለሙያ የሆኑት አቶ ተሾመ ከበደ 'የእድሜ ማጭበርበር ችግር በቀላሉ የሚታይ አይደለም' ይላሉ። በኢትዮጵያ 'የወጣቶች፣ የሴቶችና የኢትዮጵያ ሻምፒዮና' በሚል ውድድሮች ተከፋፍለው ውድድሮች ይደረጋሉ። እነዚህ በኢትዮጵያ የሚካሄዱ የወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮናም የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር መመሪያ መሰረት የሚካሄዱ ቢሆኑም እድሜን መሰረት አድርጎ እየተካሄደ እንዳልሆ ይጠቁማሉ። ከዕድሜ ጋር ተያይዞ ለሚያጋጥመው ችግር የአሰልጣኞችና የቡድን መሪዎች እንዳለ ሆኖ ከታች ከፕሮጀክት ጀምሮ ሲመለመሉ ስህተት የሚሰራበት አጋጣሚ ሰፊ እንደሆነ ባለሙያው ይገልጻሉ። የኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ስፖርት ባለሙያዎችና የክለብ ሀላፊዎች ለቀጣይ የአገሪቱ አትሌቲክስ ስፖርት ቀናኢ ከሆኑ ያገባናል፣ 'ይመለከተናል የሚሉ ከሆነ ከዚህ ተግባራቸው ሊቆጠቡ ይገባል' ሲሉ ነው የሚያሳስቡት። በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በኩልም የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት የሚጠበቅበትን ሊሰራ ይገባል ይላሉ ባለሙያው። ፌዴሬሽኑ ብቻውን ይህን ችግር ሙሉ በሙሉ ይፈታል ተብሎ ባይታሰብም ቢያንስ ግን ከዚህ በፊት ለበርካታ ጊዜ በዚህ ውድድር ላይ የሚካፈሉ ስፖርተኞችን ስም ዝርዝርና እድሜቸውም ስላለው በዚያ እንኳ ሊቆጣጠሩ ይገባል። ወጣት ስፖርተኞችን እድላቸው መዘጋት የለበትም ሲሉ ነው ሀሳባቸውን የሰጡን። አሊያ ግን ጥሩ ዝግጅት አድርገው የሚመጡ ልጆች ከእኩዮቻቸው በላይ በሆኑ ልጆች በሰፊ ርቀት ሲያሸንፉቸው የልጆቹ ሞራል የሚነካና ከስፖርቱ እንዲርቁ የሚያደርግ በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል ይላሉ። በፌዴሬሽኑ በኩልም በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን የአትሌቲክስ ስፖርት ለመገምገምና ደካማና ጠንከራ ጎኑን ለይቶ ለመስራት አስቸጋሪ ያደርግበታል። በተመሳሳይ በክለቦች በኩልም ያሉበትን ደረጃና የልጆቻቸውን አቅም ለመለካት አስቸጋሪ እንደሚያደርግባቸው ይጠቁማሉ። የኢትዮጵያ አትሌቲከስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ገብረእግዚብሔር ገብረማሪያም የእድሜ ማጭበርበር ችግሮች እንዳሉ ይናገራል። ችግሩ እስካሁን እልባት ያላገኘ መሆኑን የሚገልጸው ገብረእግዚአብሔር፤ ክለቦችና ክልሎች ኃላፊነት ተሰምቷቸው ችግሩን ለመከላከል ከፌዴሬሽኑ ጋር ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው ይናገራል። 'ስፖርተኞች ወደ ክለብ ሲቀላቀሉ ባላቸው እድሜ መሰረት መመዝግብና በተባለው የእድሜ ደረጃ ልክ  ይዘው ለመቅረብ ከፌዴሬሽኑ ይልቅ ለእነሱ የሚቀል ጉዳይ ነው። ይሁን እንጂ በክለቦችና በክልሎች በኩል ከዚህ በተቃራኒው ለውድድር ሲባል ስፖርተኞች እድሜአቸውን ቀንሰው እንዲመዘገቡ ያደርጋሉ' ሲል ነው የተናገረው። ከዕድሜ ክልል ውጭ የሆነ ተወዳዳሪ ይዞ መቅረብ በክለቦችና በክልሎች ዘንድ እየተለመደ መጥቷል። ችግሩ ከመሻሻል ይልቅ እየባሰበት ነው። በርግጥ የዕድሜ ተገቢነት የሌለው ተወዳዳሪ ይዞ መቅረብ የወቅታዊ ደስታ ቢያመጣ ከአቻቸው በላይ ተወዳድረው ብቃት እያላቸው ከሜዳ የሚያርቃቸው ተተኪ ስፖርተኞች ብዙ ስለሆኑ የነገ ተስፋ የሆኑ ታዳጊ አትሌቶች እንዳይደፈቁ ለመከላከል አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት ለመፍትሄው ተቀናጅተው መስራት ይኖርባቸዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም