በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የተጀመሩ ውይይቶች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው - ዲያስፖራዎች

70
አዲስ አበባ ግንቦት 22/2010 በአገራዊ ጉዳይ ላይ የተፈጠሩ መነቃቃቶችን ይበልጥ ለማገዝ ከዲያስፖራው ጋር የተጀመሩ ውይይቶች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢዋ ያሉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ገለጹ። ዲያስፖራዎቹ ይህንን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በውጪ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ባቀረቡት ጥሪ ዙሪያ ለመነጋገር በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ ነው። የኤምባሲው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ከፍል ኃላፊ  አቶ ተስፋዬ ወልዴ እንዳሉት መድረኩ በኢትዮጵያ ላይ ሁሉም በባለቤትነት የሚንቀሳቀስበትን ሁኔታ ለመፍጠር ታስቦ የተዘጋጀ ነው። ምሁራን፣ የተለያዩ የኮሚኒቲ አባላት፣ በመንግስት ላይ ቅሬታ አለን የሚሉ ወገኖች እንዲሁም ወጣቶች ተሳታፊ በሆኑበት በዚሁ መድረክ ላይ በአገራዊ ጉዳይ ላይ የተለያዩ አስተያየቶችና ቅሬታዎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል። በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ላሉ ስራዎች ዕውቅና ልንሰጥ ይገባል፤ ወጣቱን ለስራ፣ ለኃላፊነትና ለአመራር ለማብቃት ሰፊ ስራ መሰራት ይኖርበታል፤ በአገር ቤት ደረጃ የዲያስፖራ ተቋም ቢቋቋም መልካም ነው የሚሉ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ላይ አጽንኦት ሰጥተው ተነጋግረዋል። የውይይት መድረኩን የመሩት አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን በአንድነት አገር እንገነባለን የሚለው መንፈስ ትልቅ ተስፋ ነውና ሊበረታታ ይገባል፤ ''በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ለውጥ የእርቅና የሰላም ጥያቄ ነው፤ ወደኋላ በመሄድ መቋሰላችንን ትተን ወደፊት መራመድ ይገባናል ''ብለዋል። የምንገነባው አገር ስለሆነ ለመጪው ትውልድ ጠባሳ ሳንጥል መጓዝ ይገባናል ሲሉ ማሳሰባቸውን በሰሜን አሜሪካ የኢዜአ ወኪል ዘገባ ያመለክታል። ተመሳሳይ መድረኮች በቅርቡ በሂውስተን ቴክሳስ፣ በሚኒሶታና በአትላታ የተካሄዱ ሲሆን ከኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ጋር በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚደረገው ውይይት በሌሎችም የአሜሪካ ግዛቶች እንደሚቀጠል ከኤምባሲው የተገኘው መረጃ ያሳያል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም