ከጉጂ ዞን የተገኙ ልዩ ተሰጥኦና ችሎታ ያላቸው የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እውቅና ተሰጣቸው

57

ነገሌ የካቲት 28/2011 ከጉጂ ዞን የተገኙ ልዩ ተሰጥኦና ችሎታ ያላቸው 13 የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በትምህርት ሚኒስቴር እውቅናና የምስክር ወረቀት ተሰጣቸው።

በዞኑ ሀረቆሎ ከተማ ትናንት በተዘጋጀው መርሃ ግብር እውቅናና የምስክር ወረቀት የተሰጣቸው በሐዋሳ ዩኒቨርስቲና አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የዞኑ ተወላጅ ለሆኑ ተማሪዎች ነው፡፡

የሚኒስቴሩ ተወካይ አቶ አብዲሳ ሮባ በስነ ስርዓቱ ወቅት እንዳሉት በሳይንስና ቴክኖሎጂ በመታገዝ የሀገሪቱን እድገትና ልማት ለማፋጠን የፈጠራና የልዩ እውቀት ባለቤቶችን ለማበረታታት እየተሰራ ነው።

በመርሃ ግብሩ እውቅና ከተሰጣቸው ተማሪዎች መካከል የሂሳብና ኬሚስትሪ ልዩ ተሰጥኦና ችሎታ ላላቸው ሶስት ተማሪዎች በካናዳና በጀርመን የትምህርት እድል መስጠቱን አስታውቀዋል፡፡

የጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሮባ ተርጫ  በበኩላቸው ልዩ ችሎታና የፈጠራ ስራ ከሰላማዊ መማር ማስተማር የተገኘ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።

በስነ ምግባር የታነጸና በእውቀት የበለጸገ ዜጋ ለማፍራት በመንግስት የሚደረግ ሁለንታዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

ከፈጠራ ስራዎቹ ባለቤቶች መካከል ተማሪ ኦዳ ቦረማ በሰጠው አስተያየተ "መንግስት ለአዕምሯችን ውጤት እውቅናና የምስክር ወረቀት መስጠቱ ለበለጠ ስራ ያነሳሳናል" ብሏል።

ሌላው የፈጠራ ስራ ባለቤት  ተማሪ ሙርከታ ቢርቢርሳ በበኩሉ የውጭ ምንዛሪን የሚያሰቀሩ የፈጠራ ስራዎችን ለመስራት ፍላጎት እንዳለው ተናግሯል።

እውቅናና የምስክር ወረቀት ከተሰጣቸ ተማሪዎች ውስጥ አስሩ ከወዳደቀ ቁሳቁስ  አውሮፕላንና የግብርና መሳሪያዎች የፈጠራ ስራ የሰሩ መሆናቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም