''ሴቶች የተጣለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት የመንፈስና የዓላማ ቁርጠኝነትን መሰነቅ አለባቸው'' ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ

142

አዲስ አበባ የካቲት 28/2011 በኢትዮጵያ በተለያየ ኃላፊነት ላይ የሚገኙ ሴቶች ለትውልድ የሚተርፍ ተግባር መፈፀም ይችሉ ዘንድ የመንፈስና የዓላማ ቁርጠኝነትን ሰንቀው መሥራት እንዳለባቸው ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሰራተኞች  "የላቀ ትኩረትና ቁርጠኝነት ለሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት" በሚል መሪ  ሃሳብ የዓለማቀፍ የሴቶችን ቀንን ዛሬ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች አክብረዋል።

በበዓሉ ላይ የተገኙት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ  ለሰራተኞቹ ተመክሯቸውን በማቅረብ የማነቃቂያ ንግግር  አደርገዋል።

በዚሁ ንግግራቸው ሴቶች በመንግስትና በሌሎች ዘርፎች የተጣለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ብዙ መሰናክሎችን ለማለፍ በቆራጥነት መትጋት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ መክረዋል።

ለረጅም ዓመት አገራቸውን በዲፕሎማትነት ያገለገሉት ፕሬዝዳንቷ "በተለይ ሴት ዲፕሎማት ሆና የአገሯን ጥቅም ለማስጠበቅ በተለያዩ የዓለም ከፍሎች ኃላፊነት ተሰጥቷት ስትሰማራ የመንፈስና የዓላማ ቁርጠኝነትን መሰነቅና ለሌሎች ሴት እህቶቿና ልጆቿ አርአያ መሆን አለባት" ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ አክለውም ሴቶች በመንግስትና በህዝብ የተሰጣቸውን ኃላፊነት አለመወጣት ወደፊት የሚመጡ ሴቶችን እድል የመዝጋት ያህል እንደሆነ አሳስበዋል።

አገራቸውን በዲፕሎማትነት ባገለገሉባቸው ረጅም ዘመናት ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎችን እንዳለፉ የተናገሩት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ "የዛሬዎቹ አገር ተረካቢ ሴቶች የዓላማ ጽናትን አንግበው ለትወልድ የሚተርፍ ስራ መስራት አለባቸው" ብለዋል።

ሴቶች በስራቸው ሁሉ የወንድ አጋርነትን በማመን በትብብርና በመከባበር መስራት ለውጤት እንደሚያበቃቸውም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ሴቶችን ማብቃትና የኢኮኖሚ ችግሮቻቸውን በመፍታት ብቁ ዜጋ ለማድረግ "አሁን በስልጣን ላይ ያለን ሴት አመራሮችና ወንድ አጋሮቻችን ከፍተኛ ሚና መወጣት አለብን" ብለዋል።

በተለይ በኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ገብተው ትምህርታቸውን አቋርጠውና አማራጭ አጥተው ህይወታቸውን ለአደጋ በሚዳርግ ሥራ ተሰማርተው ብቁ ዜጋ የመሆን እድላቸውን የሚያጡ ሴቶችን ልንታደጋቸው ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

በዩንቨርስቲ ውስጥ የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸውን ሴቶች ለማገዝና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሚመለመሉ ሴት ዲፕሎማቶች ያላቸውን ልምድ ለማካፈል ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ቃል ገብተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሒሩት ዘመነ በበኩላቸው በአገሪቱ የሴቶች ተሳትፎ በማድግ ላይ ነው ብለዋል።

እድሉ የተሰጣቸው ሴቶች መስራት እንደሚችሉ በተቋማቸወም ሆነ በአገራቸው ላይ እያሳዩ እንደሆነም አብራርተዋል። 

የሴቶች ቀን የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት የበለጠ ለማሳደግና በውጭ አገር የመብት ጥሰት የሚፈጸምባቸውን ሴቶች ለመታደግ ህብረት ለመፍጠር ያግዘናል ነው ያሉት።

በዕለቱ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ የሴቶችን ችግሮች ለመፍታት  በሚቻልበት መንገድ ላይ ያተኮረ ፅሁፍ አቅርበው ውይይት ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም