ለተፈናቃዮች መቋቋሚያ 80 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ ንቅናቄ ተጀመረ

79

ጎንደር የካቲት 28//2011 በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በጊዚያዊ መጠለያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያስፈልገውን 80 ሚሊዮን ብር ከህዝቡ ለማሰባሰብ ንቅናቄ መጀመሩን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አስታወቁ፡፡

ተፈናቃዮችን ለማቋቋም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በዞን ደረጃ የተቋቋመው ግብረ ኃይል ትናንት በጎንደር ከተማ የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡

የምክክር መድረኩን የመሩት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ጣምያለው እንደተናገሩት ክረምቱ ከመግባቱ በፊት ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል የማስፈጸሚያ ዕቅድ በዞን ደረጃ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

በዕቅዱ መሰረትም የአካባቢው ሕብረተሰብ፣ ባለሀብቶች፣ የመንግስት ሠራተኞችና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የገንዘብ፣ የቁሳቁስና የጉልበት ድጋፍ የሚያበረክቱበት ህዝባዊ ንቅናቄ በየደረጃው ተጀምሯል፡፡

በዞኑ 14 ወረዳዎች ህዝባዊ ንቅናቄውን የሚያስተባብሩ ኮሚቴዎች መቋቋማቸውን የጠቆሙት ዋና አስተዳዳሪው ለተፈናቃዮች መቋቋሚያ እንዲውል የሚያስፈልገውን 80 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ ወደተግባራዊ ሥራ ገብተዋል፡፡

አቶ ብርሃኑ እንዳሉት በህዝብ ንቅናቄ ለማሰባሰብ የታቀደው ገንዘብ ለተፈናቃዮች ቤት ገንብቶ ለማስረከብ፣ ለምርጥ ዘር፣ ለማዳበሪያና ለእርሻ መሳሪያዎች ግዢ የሚውል ነው፡፡

በተበታተነ መንገድ ሲካሄድ የቆየው የድጋፍ ማሰባሰብ ሥራ በቀጣይ ተጠያቂነት በሰፈነበት አሰራር በኮሚቴው እውቅና ብቻ የሚካሄድ እንደሚሆንም ገልጸዋል፡፡

አብዛኞቹ ተፈናቃዮች አርሶአደሮች መሆናቸውን ጠቁመው ክረምቱ ከመግባቱ በፊት የዘር፣ የማዳበሪያ፣ የእርሻ መሳሪያና የእርሻ በሬ ድጋፍ በማድረግ ወደ ግብርና ስራቸው ለመመለስ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መንበሩ አውደው በበኩላቸው መኖሪያ ቤታቸው ለተቃጠለባቸው ተፈናቃዮች ቤት ሰርቶ ለማስረከብ የክልሉ መንግስት የቤት ክዳን ቆርቆሮ ለማቅረብ ቃል መግባቱን ተናግረዋል፡፡

እስካሁን በተከናወነው የልየታ ሥራ ከ4 ሺህ በላይ ቤቶች በግጭቱ መቃጠላቸውን የጠቆሙት ኃላፊው የተፈናቃዮችን ትክክለኛ ቁጥር ዳግም የማጣራት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የጭልጋ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አቡሃይ አምላኩ በበኩላቸው በወረዳው በግጭቱ ሳቢያ 2ሺህ 500 ቤቶች በከፊልና በሙሉ የመቃጠል አደጋ እንደደረሰባቸው ተናግረዋል፡፡

"ተፈናቃዮችን ለማቋቋም በሚደረገው የተቀናጀ ርብርብ ወረዳው የቤት መስሪያ ቦታ ልየታና ሽንሸና ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ጀምሯል" ብለዋል፡፡ 

አብዛኛው የተፈናቀለው ህዝብ በግጭቱ የእርሻ መሳሪያውንና የእርሻ በሬዎቹን ጭምር ማጣቱን ገልጸው፣ ወደ ግብርና ሥራው ለመመለስ ድጋፍ የማሰባሰብ ስራውን ወረዳው አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

የዞኑ አዴፓ ተወካይ አቶ ካሳሁን ንጉሴ በበኩላቸው "በህዝቡና በመከላከያ ሠራዊት የጋራ ጥረት በአካባቢው የሰፈነው አንጻራዊ ሰላም ዘላቂነት እንዲኖረው የተጀመሩ የሰላም ጥረቶች ተጠናከረው መቀጠል አለባቸው" ብለዋል፡፡

የሀብት አሰባሰቡም በተገቢው መንገድ መመራት እንዳለበት ጠቁመው በክረምት ወራት ተሽከርካሪ በማያስገቡ አካባቢዎች መጠባበቂያ ሊሆን የሚችል የእርዳታ እህል ቀደም ብሎ ሊጓጓዝ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ከዞኑ አደጋ መለካለልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ከምዕራብ ጎንደር ዞን ተፈናቅለው የመጡትን ጨምሮ በዞኑ በ13 ጊዚያዊ መጠለያዎች 50ሺህ የሚጠጉ ተፈናቃዮች ይገኛሉ፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም