ሦስተኛው ሀገር አቀፍ የሴቶች ጫዋታ በጅግጅጋ ስታድየም ዛሬ ተጀመረ

418

ጅግጅጋ የካቲት 28/2011 ሦስተኛው የመላ ኢትዮጵያ የሴቶች ጨዋታ ተሳታፊ የስፖርት ቤተሰቦች የህዝቦች አንድነትና ትስስር እንዲጠናከር መስራት እንደሚገባቸው የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሒሩት ካሳው አሳሰቡ።

”ስፖርት ለሴቶች ሁለንተናዊ ለውጥ”  በሚል በመሪ ሃሳብ ሦስተኛው ሀገር አቀፍ የሴቶች ጫዋታ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በጅግጅጋ ስታዲየም ተጀመሯል።

በውድድሩ መክፈቻ ላይ ሚኒስትሯ እንደተናገሩት ሴቶች በስፖርቱ ዘርፍ በዓለም አቀፍ መድረክ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ አድርገዋል።

“የዚህ ውድድር ተሳታፊዎችም ከጫዋታው ጎን ለጎን ኢትዮጵያዊ ፍቅርና ጫዋነት፣ ባህላዊ ትስስርና አንድነት ጎልቶ የሚያወጡ ስራዎች መከናወን ይኖርባቸዋል” ብለዋል።

“ኢትዮጵያ በእናት ትመሰላልች እኛ ሴቶች በተሰጠን ኃላፊነት ስኬታማ በመሆን የሀገራችን የኩራት ምንጭ ልንሆን ይገባናል” ያሉት ዶክተር ሒሩት መድረኩ ለህዝቦች መቀራረብና ትስስር መጠናከር እንደሚረዳ ገልጸዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስተፌ ሙሀመድ ውድድሩ በክልሉ መዘጋጀቱ በክልሉ አንዳንድ ከተሞች በተከሰተው ብጥብጥና ረብሻ ምክንያት የተጎዳውን ገጽታ ለመገንብት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ያዘጋጀውን ሀገር አቀፍ የሴቶች ውድድር በስኬት ለማስተናገድ በጀት ከመመደብ ጀምሮ የውድድር ስፍራዎችና ስታድየሙን የመጠገን ስራ መከናወኑን አስረድተዋል።

በመሆኑም ለተሳታፊዎች በቂ የውድድር ስፍራዎች መዘጋጀታቸውንና የእንግዶች ማረፊያ ስፍራዎችም መመቻቸታቸውን ገልጸዋል።

የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ እርስቱ ይርዳ በበኩላቸው ተወዳዳሪዎች በጅግጅጋ ከተማ ቆይታቸው ሴቶች በስፖርታዊ ውድድሮች ላይ በትብብርና በመግባባት ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያሳድጉ ጠይቀዋል።

በጨዋታው ለመሳተፍ የተገኙት አንድ ሺህ 642 ሴት ስፖርተኞችና የስፖርት አመራሮች በውድድሩ ወቅት ስፖርታዊ ጫዋነትን እንዲያሳዩም መክረዋል።

በመክፈቻው ላይ በቤንሻንጉልና አስተናጋጅዋ ሶማሊ ክልል መካከል በተካሄደው የእግር ኳስ ጫዋታ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሶማሊ ክልልን አምስት ለአንድ አሸንፏል።

ለእስር ቀናት ከሚካሄዱት ጨዋታዎች መካከል እግር ኳስ፣ ቮሊቦል፣ ቅርጫርት ኳስ፣ ገመድ ጉተታ፣ አትሌቲክስና ፓራሊምፒክ ይገኙበታል።