በክልሉ የወጣቱን የሥራ አጥነት ችግር ለመፍታት የተሰራው ሥራ ደካማ ነው….የአማራ ክልል ምክር ቤት

727

ባህር ዳር የካቲት 28/2011 በአማራ ክልል የወጣቱን ስር የሰደደ የሥራ እጥነት ችግር ለመፍታት የተሰራው ሥራ ደካማ ነው ሲል የክልሉ ምክር ቤት ገመገመ፡፡

ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎ የክልሉን የቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዞች ልማት የሥራ አፈፃፀም ገምግሟል፡፡

በግምገማውም የሥራ እድል ፈጠራው የወጣቱን ችግር በሚፈታ መንገድ በተደራጀ አግባብ እየተከናወነ አለመሆኑን ለይቷል፡፡

“ለወጣቱ እየተሰጠ ያለው ብድር፣ የገበያ ትስስር፣ የቦታ አቅርቦት፣ ስልጠና፣ የቴክኖሎጂ አቅርቦትና መሰል ችግሮች አሁንም ወጣቱን ተስፋ እያስቆረጡት ይገኛል” ሲልም ምክር ቤቱ የጋራ ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡

ለሚገነቡ ሼዶች መሰረተ ልማት አለመሟላት፣ ኢንተርፕራይዞች በመንግስት ፕሮጀክቶች እንዲሳተፉ አለማድረግና የመብራት አቅርቦት አለመሟላት የሥራ እድል ፈጠራው ውጤታማ እንዳይሆን እንቅፋት ሆነዋል፡፡

ለተጠቃሚዎች የተሰጠ ብድርን በባለቤትነት ተከታትሎ በማስመለስና በመሳሰሉት ችግሮች ላይ በየደረጃው ያለው አመራር ጉዳዩን በባለቤትነት ተከታትሎ እየመረው እንዳልሆነም ምክር ቤቱ ገምግሟል፡፡

የክልሉ ቴክኒክ፣ ሙያና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ የሻምበል ከበደ በበኩላቸው እንዳሉት የሥራ እድል ፈጠራውን አመራሩ የኔ ብሎ ተቀብሎ እየተገበረው አይደለም፡፡

በገጠርና በከተማ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሥራ ፈላጊ መኖሩን የገለጹት ኃላፊው “በአመራሩ በኩል ስራውን የመግፋት፣ በአንድ ተቋም ብቻ እንዲሰራ ፍላጎት የማሳየትና የመተግበር ችግር አለ” ብለዋል፡፡

በሥራ ዕድል ፈጠራው በትክክል ሥራ ፈላጊዎች ተጠቃሚ እየሆኑ እንዳልሆነ ገልጸው በዘርፉ ባለሃብቱ ተደራጅቶ መግባት፣ በቤተሰብ መደረጃት፣ አመራሩ ጭምር ተሳታፊ ሆኖ መገኘት የተስተዋሉ ችግሮች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

“ከእዚህ በተጨማሪ ነጋዴው ንግድ ፈቃዱን ሳይቀር መልሶ በጥቃቅን መደራጀት፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ጭምር ተደራጅተው ብድር ወስደው መገኘታቸው የአሰራር ክፍተቱን ያሳያል” ብለዋል አቶ የሻምበል ፡፡

በመሆኑም መንግስት ለወጣቱ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያለው ፍላጎት ከሥራ እጥ ወጣቱ ቁጥር ጋር ሲነፃፀር የሥራ እድል ፈጠራው ችግር ውስጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና የመሰረተ ልማቶች እጥረት የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራው በሚፈለገው ደረጃ እንዳይንቀሳቀስ ማድረጋቸውንም ጠቁመዋል፡፡

አቶ የሻምበል እንዳሉት በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመት አዳዲስ ኢንተርፕራይዞችን በማቋቋም ለ746 ሺህ ዜጎች በከተማና በገጠር የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ ማከናወን የተቻለው የዕቅዱን 18 ነጥብ 8 በመቶ ብቻ ነው፡፡

ወደ ሥራ ለገቡ አዲስና ነባር ኢንተርፕራይዞችም ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር የተሰጠ ሲሆን ቀደም ሲል ከተሰጠው 196 ሚሊዮን ብር 99 በመቶ ብድር ማስመለስ ተችሏል፡፡

“በቀጣይ የአሰራር ክፍተቶችን በመለየት በተለይም ከፍተኛ የሥራ እጥ ቁጥር ያለባቸውን ባህር ዳር፣ ጎንደርና ደሴ ከተሞችን በተለየ ሁኔታ ለመደገፍ እንቅስቃሴ ተጀምሯል” ብለዋል፡፡

የስራ እድል ፈጠራው ውጤታማ ይሆን ዘንድም የምክር ቤት አበላትም ሆኑ በየደረጃው የሚገኘው አመራር በባለቤትነት ሊሰራ እንደሚገባው አቶ የሻምበል አሳስበዋል፡፡

የሥራ ዕድል ፈጠራ ሪፖርቱ በምክር ቤት አባላት ተገምግሞ በአብላጫ ድምጽ የፀደቀ ሲሆን በነገው እለትም ምክር ቤቱ በሌሎች አጀንዳዎች እንደሚመክር ለማወቅ ተችሏል፡፡