ቀጣናዊ ትብብርን ከማጠንከር አንፃር ጎልቶ እየታየ ያለው የኢትዮጵያ ሚና

674

በኢዜአ ሞኒተሪንግ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የምስራቅ አፍሪካ ጉብኝትን አስመልክተው የሃገር ውስጥም ሆኑ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የተለያዩ ዘገባዎችን አውጥተዋል። መገናኛ ብዙሃኑ በቀጠናው በሚገኙ ሃገራት መካከል የተፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመቅረፍ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተጫወቱት የሚገኘውን ሚና ትልቅ እንደሆነም የዘገባቸው አካል አድርገውታል።

የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የኢትዮጵያ የሶስት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት፣ የሶማሊያው ፕሬዚዳንት አብዱላሂ ፎርማጆ ተመሳሳይ የጉብኝት መርሃ ግብርም የቀጣናውን ሰላም ከማስከበር አንፃር ታልሞ የተካሄደ እንደሆነም መገናኛ ብዙሃኑ ሳይጠቅሱ አላለፉም።

ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ኬንያ ምጣኔ ሃብታዊ ትብብር ለመፍጠር የሚያስችላቸውን ውይይት አደረጉ በማለት ዘገባውን ያወጣው ቦርከና ድረ ገፅ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሶስት ቀናት የኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝታቸውን ማጠናቀቃቸውን አስነብቧል።

እንደ ድረ ገፁ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ በሶስት ቀናቱ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ለኬንያውያን ባለሀብቶች በተዘጋጀ የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ከተገኙ በኋላ ሃዋሳ እና አርባምንጭን የጎበኙ ሲሆን ከአዲስ አበባ ሰሜን አቅጣጫ 120 ኪሎሜትር ላይ በምትገኘው ደብረ ብርሃን ከተማ የኢንዱስትሪያል ፓርክ መርቀው ከፍተዋል።

አፍሪካ ኒውስ በበኩሉ በኢትዮዽያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አደራዳሪነት የኬንያና የሶማሊያ መሪዎች ተገናኝተው እንዲወያዩ በመደረጉ የሁለቱ ሃገራት ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት እንዲለዝብ ምክንያት መሆኑን ዘግቧል።

ሶማሊያና ኬንያ የነበረባቸውን ቁርሾ አስወግደው በቀጣናው ሰላማዊ አየር እንዲነፍስ የራሳቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም ነው አፍሪካ ኒውስ ያመለከተው። ሁለቱ ሃገራት ባለፈው ወር ነበር የባህር ድንበር ይገባኛል ውዝግብ ውስጥ ገብተው አምባሳደሮቻቸውን ከያሉበት ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ያደረጉት፤ ብሏል ዘገባው።

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስተባባሪነትም የሶማሊያው ፕሬዚዳንት አብዱላሂ ፎርማጆ እና ኡሁሩ ኬንያታ ናይሮቢ ውስጥ ተገናኝተው ሊወያዩ መቻላቸውን ያነሳው የቢቢሲ የአማርኛ ዘገባ የሶማሊያ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለቱ ሃገራትን በማደራደር ለነበራቸው ሚና ምስጋናውን በመግለጫ አስደግፎ እንዳስተላለፈ አክሏል።

ኬንያና ሶማሊያ ፍሬያማ ውይይት ማካሄዳቸውን የገለፀው የሶማሊያ መንግስት መግለጫ ሃገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማደስና ለማጠናከር መስማማታቸውን አስቀምጧል። እንደ ቢቢሲ ዘገባም ሶማሊያ፣ ኬንያ የይገባኛል ጥያቄ እያነሳችበት የሚገኘው የባህር ድንበር ጉዳይ ለአለም አቀፉ ፍትህ ፍርድ ቤት አቅርባ ውጤቱን እየተጠባበቀች ትገኛለች።

የሶማሊያና የኬንያ መንግስታትን የባህር ድንበር ውዝግብ ለማደራደር የኢትዮዽያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ናይሮቢ መግባታቸውን የዘገበው ዘ ኢስት አፍሪካን የባለፈው ሳምንት የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የአዲስ አበባ ጉብኝት በጉዳዩ ዙሪያ ለመመካከር እንደሆነም በዘገባው አስፍሯል።

ዘ ኢስት አፍሪካን ቀጥሎ ባወጣው ሌላው ዘገባው ደግሞ ኬንያና ሶማሊያ በአካባቢው ሰላምን ለማስፈን የሚያስችል ስምምነት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አደራዳሪነት መስማማታቸውን የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮን መረጃ ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።

ፐሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታና የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሞሃመድ ፎርማጆ በህንድ ውቅያኖስ አካባቢ ባለ የባህር ድንበር ይገባኛል ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን የፃፈው ዘ ስታር የሀገራቱ መሪዎች ድርድርንም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሊቀመንበርነት እንደመሩት አስነብቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሁለቱ ሃገራት በቀጣናው ሰላምን ለማስፈን የሚያስችሉ እርምጃዎችን ለመውሰድ መስማማታቸውን ዘ ስታር ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዊተር ገፅ ላይ በመውሰድ ዘግቦታል።

የኬንያው ቢዝነስ ዴይሊ አንድ የሶማሊያ ዲፕሎማትን ዋቢ በማድረግም የሁለቱ ሃገራት የባህር ድንበር ጉዳይ ሊፈታ የሚችለው በአለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት መሆኑን የገለፁለትን ይዞ ወጥቷል፡፡

ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ደቡብ ሱዳን በቀጣናው በሁሉም ዘርፎች አብረው ለመስራት የሚያስችላቸውን የትብብር ስምምነት በደቡብ ሱዳኗ ከተማ ጁባ መድረሳቸውን የዘገበው ኒውስ ጋና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይና የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ  ለደቡብ ሱዳን ሰላም ገንቢ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ የደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ንሂያል ዴንግ ንሂያልን ጠቅሶ ሃተታውን አድርሷል።

የቀጣናውን ሰላም አስተማማኝ በማድረግ ለየሃገራቱ ህዝቦች ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊና ፖለቲካዊ ዕድገት የበኩሉን ሚና ሊጫወት እንደሚችል በታመነበት የሃገራቱ ቅርርብ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እየደረጉት ያለው ጥረት ሊበረታታ እንደሚገባው በአካቢው ሃገራት የሚገኙ መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ ሌሎች አለም አቀፍ የሚዲያ አካላት መልዕክታቸውን አሰራጭተዋል።