የአሜሪካ መንግስት ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ በተስፋፋባቸው የኢትዮጵያ ወረዳዎች ሊያካሄድ ያሰበውን ዕቅድ ይፋ አደረገ

4511

አዲስ አበባ ግንቦት 22/2010 የአሜሪካ መንግስት ኤች.አይ.ቪ/ ኤድስ በተስፋፋባቸው 312 የኢትዮጵያ ወረዳዎች በሽታውን ለመከላከልና ለህሙማኑም ድጋፍ ለማቅረብ የሚያስችል ዕቅድ ይፋ አደረገ።

በአሜሪካ መንግስት ድጋፍ የሚተገበረውና በኤች.አይ.ቪ/ ኤድስ ጉዳይ ላይ አትኩሮ ድጋፍ የሚሰጠውን ዓለማቀፍ መርሃ-ግብር (ፔፕፋር) 15ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ መግለጫ ተሰጥቷል።

በመርሃ-ግብሩ አማካኝነት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበር  ኤች.አይ.ቪ/ ኤድስን ለመከላከል ሊሰሩ የታቀዱትን ተግባራት ይፋ ሆነዋል።

በዕቅዱ መሰረት የቫይረሱ ስርጭት ተስፋፍቶባቸዋል ተብለው በተለዩት ወረዳዎች የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም የቅድመ-መከላከል ስራ እንዲጠናከር ይደረጋል ተብሏል።

የመርሃ ግብሩ አስተባባሪ አምባሳደር ዲቦራህ ሊ ብርክስ እንዳሉት ህዝቡ የኤች.አይ.ቪ/ ኤድስ ምርመራ በማካሄድ የጤንነቱን ሁኔታ እንዲገነዘብ ከማስቻል ባሻገር ከቫይረሱ ጋር ለሚኖሩት ልዩ እንክብካቤና ድጋፍ አገልግሎት እንዲመቻች ይደረጋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የኤች.አይ.ቪ/ ኤድስ ጉዳይን በተለያዩ የአገሪቱ ተቋማት የሥራ ተግባራት ውስጥ እንደ አንድ ዋና አጀንዳ ሆኖ  እንዲካተት ማድረጉን አምባሳደሯ አድንቀዋል።

ኢትዮጵያ በሽታውን ለመከላከል የቀረፀችው ዕቅድ ለሌሎች የአፍሪካ አገራትም ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በዚሁ መርሃ-ግብር አማካኝነት ላለፉት 13 ዓመታት ለተከናወኑት ተግባራት የአሜሪካ መንግስት ከ2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ አድርጓል።

በቅርቡ ይፋ በሆነ መረጃ በኢትዮጵያ 718 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ከኤች.አይ.ቪ/ ቫይረስ በደማቸው ሲገኝ  በየዓመቱም 20 ሺህ የሚሆኑት በበሽታው ምክንያት ለህልፈት ይዳረጋሉ።

በአገሪቱ ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ ህፃናት አሉ ተብሎ ሲገመት፤ ከእነዚህ ውስጥ 800 ሺህ ያህሎቹ ወላጆቻቸውን የተነጠቁት በኤድስ መሆኑም ይነገራል።