በሰላም ግንባታና ግጭት መከላከል ላይ ያተኮረ የ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

63

አዲስ አበባ  የካቲት 28/2011 በኢትዮጵያ የመልካም አስተዳድር፣ ግጭት መከላከልና ሰላም ግንባታ ላይ ያተኮረ የ2 ነጥብ 8 ሚሊዬን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ።

ፕሮጀክቱ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰላም ግንባታ ፈንድ አማካኝነት ከተለያዩ ኤጀንሲዎቹ በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ ሥራ ላይ ይውላል ተብሏል። 

የሶሰት ዓመታት አድሜ ያለው ፕሮጀክቱ ዓላማ በኢትዮጵያ የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ለማፋጠን አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንደሆነም ተጠቅሷል።

የሰላም ሚኒስቴር ከሴቶችና ወጣቶች እንዲሁም ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን ፕሮጀክቱን ያስፈጽሙታል።

የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በዚህ ወቅት እንዳሉት ድጋፉ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለተቋቋመበት ዓላማና ለሚያስፈጽማቸው ተልዕኮዎችን ስኬት ሚናው የጎላ ነው።

ፕሮጀክቱ በዋናነት የህግ የበላይነት፣ ግጭት መከላከልና አፈታት፣ ዕርቅ ሰላም፣ የሰላም ግንባታ እንዲሁም አፋጣኝ አገራዊ የሰላም ግንባታ ስትራቴጂ ለመቅረጽ ያለመ መሆኑን አንስተዋል።

ግጭት በሚቀሰቀስባቸው የክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ተፈናቃዮችን ማቋቋም፣ ለወጣቶችና ሴቶች ገቢ የሚያገኙበት ሁኔታ ማመቻቸትና የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች የፕሮጀክቱ አካላት ናቸው።

ለአብነትም በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ ለሚከሰቱ ገጭቶች ማህበረሰቡንና አገር በቀል የግጭት አፈታት ስርዓትን ያካተቱ ውይይቶች ለማድረግ፣ የግጭቱን መንስኤ መለየትና ማህበረሰብ አቀፍ የግጭት መከላከል ስርዓት ለመዘርጋት እንደሚውል ተገልጿል።

ኢትዮጵያ ወጥ አገራዊ የሰላም ግንባታ ስትራቴጂ እንዲኖራት ማድረግ የፕሮጀክቱ ዓላማ መሆኑን ወይዘሮ ሙፈሪሃት ገልጸው፤ ድጋፉን ላደረጉ ዓለም አቀፉ የልማት ፕሮግራምና አጋር ድርጅቶች ምስጋና አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል ሰላማዊና ዘላቂ ሰላም ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትሯ፣ ለሰላም መሰረተ ልማት ዝርጋታ የሁሉም የልማት አጋር አካላት ትብብር እንደሚሻ ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ የመንግስታቱ ድርጅት ሰብዓዊ ዕርዳታ አስተባባሪ አኔስ ቹማ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እያካሄደችው ካለወ ለውጥ ጋር ሰላም፣ መረጋጋትና ደህንነት ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ይህ ደግሞ ተመድ፣ መንግስትና ህዝቡ የሚጋሩት ሃላፊነት ነው ብለዋል።

በማህበረሰቡ ውስጥ ግጭትን ለመካለከልና ሰላምን ለማረጋገጥ አካታች የሴቶችና ወጣቶች ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሰላም ግንባታ የሴት ካበኒዎችን መሰየማቸውን አድንቀዋል።

ድጋፍም ኢትዮጵያ አገራዊ የሰላም ግንባታ ስትራቴጂ እንዲቀረጽና ለገጠማት ወቅታዊ የዜጎች መፈናቀል ችግሮች በጥናት ላይ የተመሰረተ  መፍትሄ እንዲበጅላቸው ያለመ መሆኑን ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም