ሴቶች የለውጡ እንቅፋቶችን ለማስወገድ የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው--- ወይዘሮ ጠይባ ሀሰን

171

አዳማ  የካቲት 28/2011 ሴቶች የለውጡ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ  ጎጂ አስተሳሰቦችና ተግባራትን ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዘዳንት ወይዘሮ ጠይባ ሀሰን አሳሰቡ።

" ሀገራዊ የሴቶች ንቅናቄ ለዘላቂ ሰላም " በሚል መሪ ሀሳብ የዓለም የሴቶች ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ  ዛሬ በአዳማ ከተማ ተከብሯል።

ወይዘሮ ጠይባ ሀሰን  በበዓሉ ላይ  ባደረጉት ንግግር  " የሀገራችን  የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በፅኑ መሰረት ላይ ለማኖር ሴቶች የለውጡን እንቅፋት በመታገልና በማስወገድ ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆን አለባቸው" ብለዋል።

የህብረተሰቡ ግማሽ አካል የሆኑት ሴቶች ትውልድን በማፍራትና ኮትክቶ በስነ ምግባር በማሳደግ ረገድ ልዩ ፀጋ መጎናፀፋቸውን ያመለከቱት   ምክትል ፕሬዘዳንቷ በሁሉም መስኮች እኩል በመሳተፍ ለውጡን ለውጤት ማብቃት እንደሚገባ አስገዝበዋል።

"ሴቶች የጥቁር ህዝቦች ተምሳሌት በሆነው አደዋ ጦርነት ጭምር በመሳተፍ ያስመዘገቡትን አንፀባራቂ ድል በሀገር ሰላም ግንባታና የህዝቦችን አንድነት በማጠናከር ላይ መድገም ይጠበቅብናል" ብለዋል።

ወይዘሮ ጠይባ እንዳሉት የዘንድሮ የሴቶች ቀን  ልዩ የሚያደርገው በለውጡ ሂደት ሴቶች 50 በመቶ ሀገር የመምራት ኃላፊነት ወስደው በሙሉ አቅም እየተንቀሳቀሱ ባለበት ወቅት በመሆኑ ነው።

በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ  በሁሉም የልማት መስክ በመረባረብ የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው  አሳስበዋል፡፡

"በየደረጃው ያለን የሴት አደረጃጀቶች በአካባቢያችን ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥና የህግ የበላይነት እንዲሰፍን መስራት  አለብን"  ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃም ወይዘሮ አፀደ አይዛ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ አንዳንድ  አካባቢዎች በሚስተዋለው የሰላም እጦት ተጋላጭ ሴቶችና ህፃናት በመሆናቸው የግጭት መንስኤዎችን በጋራ  መከላከል  እንደሚገባ አመልክተዋል።

የኦሮሚያ ሴቶች ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት ወይዘሮ አስካለ ለማ በበኩላቸው ሴቶች ከኋላ ቀር አስተሳሰብና አመለካከት ተፅእኖ ተላቀው በሁሉም መስክ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸው እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸዋል።

" አሁን እየተፈታተኑን ያለውን የልማት፣ሠላምና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት  በሚደረገው ጥረት ውስጥ በንቃት በመሳተፍ የፀረ ድህነት ትግሉን  ከዳር ማድርስ አለብን "ብለዋል።

በዓለም ለ108ኛ ጊዜ  በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ  ለ43ኛ ጊዜ በአዳማ በተከበረው የሴቶች ቀን በዓል ላይ ከፌዴራል ፣ ከዘጠኝ ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተወከሉ ሴቶችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም