በሚቀጥሉት ስድስት ወራት 8 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል

62

አዲስ አበባ የካቲት 28/2011 በኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት 8 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች የእለት ደራሽ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆነ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተገለጸ።

ብሔራዊ የአደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን የልማት አጋሮች፣ ለጋሾችና የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት የተረጂዎችን ቁጥር ይፋ አድርጓል።

በዚሁ ወቅት እንደተገለጸው ለተረጂዎች ድጋፍ ለማድረግ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል።

ከዚህ ውስጥ 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎች የተመጣጠነ ምግብ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን 609 ሺህ 961 የሚሆኑት ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ናቸው።

በአገሪቱ ተፈጥሮ በነበረው ግጭትና አለመረጋጋት የተፈናቀሉ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎች አስቸኳይ ምግብ እና መጠለያ ተጠቃሚ ይሆናሉ።

የጤና፣ የትምህርትና የግብርና ድጋፎች እስከ አመቱ ማጠቃለያ ድረስ እንደሚሰጥ እቅድ ተይዟል።

ኮሚሽነሩ ምትኩ ካሳ እንዳሉት በአጠቃላይ ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው ዜጎች ውስጥ 40 በመቶ ኦሮሚያ፣ 22 በመቶ ሶማሌ፣ 12 በመቶ አማራ፣ 10 በመቶ ደቡብ እንዲሁም አራት በመቶ በትግራይና አፋር ክልሎች ይገኛሉ።

ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ሃረሪ ክልሎችና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርም በእለት ደራሽ ድጋፍ የሚካተቱ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም