የኢትዮጵያና ግሪክ ንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ

117

አዲስ አበባ  የካቲት 28/2011 የኢትዮጵያ የንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት  ከግሪክ የንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ የሰነድ ስምምነት ተፈራረመ።

የኢትዮጵያ የንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ምክትል ፀሃፊ አቶ ውቤ መንግስቱ  እንደገለጹት ስምምነቱ ከግሪክ ባለሀብቶች ጋር በጋራ የንግድ ትርዒቶችን፣ ጉባዔዎችንና ስልጠናዎችን ለማዘጋጀት ያግዛል።

የቴክኖሎጂ ሽግግር ለመፍጠርና የገበያ ትስስር ለመፍጠር የሚረዱ መረጃዎችን ለመለዋወጥም እንዲሁ።

የግሪክ የንግድ ዘርፍ ማህበር ምክር ቤት የቦርድ አባል ሚስተር ጂኦርጊኦስ ዚስማቶስ ስምምነቱ የግሪክና የኢትዮጵያን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናክር እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው የግሪክ ባለሀብቶች ከምክር ቤቱ አባላት ጋር አዲስ አበባ መግባታቸውን ጠቁመዋል።

በግሪክና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ መጠን ለማሳደግም ምክር ቤቱ  ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዴዔታ ዶክተር አክሊሉ ሃይለ ሚካኤል ግሪክና ኢትዮጵያ ታሪካዊ የሆነ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ቢኖራቸውም የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስራቸው ግን ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ለንግድና ኢንቨስትመንት የተመቹ በርካታ አማራጮች መኖራቸውን ጠቅሰው የግሪክ ባለሀብቶች ይህንን እድል በመጠቀም በኢትዮጵያ መዋለ ነዋያቸውን እንዲያውሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የግሪክ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ኒኮላስ ኩዊክ በበኩላቸው አገሪቱ በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ላይ በመሆኗ የግሪክና የኢትዮጵያን የንግድ ትስስር ለማጠናክር ትክክለኛ ወቅት ነው  ብለዋል።

ግሪክ በሆቴልና ቱሪዝም፣በፋይናንስ ፣ሎጅስቲክስ፣ በትራንስፖርት፣ በሌሎች ዘርፎች ላይ ውጤታማ መሆኗን ገልጸው በእነዚህ ዘርፎች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር  ለመስራት በግሪክ በኩል ፍላጎትና ዝግጁነት መኖሩንም ጠቁመዋል።

በንግድና ኢንደስትሪ ሚንስቴር የውጭ ንግድ ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ሙሉጌታ በበኩላቸው በግሪክና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ መጠን ወደ ግሪክ ያደላ መሆኑን አንስተዋል።

ባለፉት 5 አመታት ከኢትዮጵያ ወደ ግሪክ ከተላኩ ምርቶች የተገኘው ገቢ ከ12 ሚሊዬን ብር ያልበለጠ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ የንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከግሪክ ጋር ያደረገው ስምምነት ይህንን ለማሻሻል ያግዛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም