ዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ለጋሽ አካላት በኢትዮጵያ ለተረጂዎች እንዲደግፉ ጥሪ ቀረበ

448

አዲስ አበባ የካቲት 28/2011 የኢትዮጵያ መንግሥት በተያዘው ዓመት የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ የዕለት ደራሽ ተረጂዎችን ለመደገፍ የሚያደርገውን ጥረት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ለጋሽ አካላት እንዲያግዙ ጥሪ ቀረበ።           

የብሄራዊ አደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን ዛሬ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት 8 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ይፋ አድርጓል።        

በመርሃ ግብሩ ላይ ዓለም አቀፍ ለጋሽ አካላት፣ የልማት አጋሮችና የመንግሥት ተወካዮች ተገኝተዋል።     

በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት አጋጥሞ የነበረው የኤልኒኖ ድርቅ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታዩ ግጭቶች ጋር ተዳምሮ የተረጂዎች ቁጥር ክፍ እንዲል እያደረገ ነው።  

በአሁኑ ወቅት ያለውን የተረጂዎች ቁጥር ለማወቅ በተደረገ የዳሰሰ ጥናት እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2019 ድጋፍ የሚሹ 8 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎችን የዕለት ደራሽ ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን ይፈልጋሉ።  

ከዚህ ውስጥ ኦሮሚያ 46 በመቶ፣ ሶማሌ 22 በመቶ፣ አማራ 12 በመቶ፣ ደቡብ 10 በመቶ እንዲሁም ትግራይና አፋር ክልሎች አራት በመቶ አስቸኳይ የምግብና ገንዘብ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።  

በተመሳሳይ በጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና ሀረሪ ክልሎች እንዲሀም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርም እንዲሁ እርዳታ ፈላጊዎች እንደሚገኙ ነው የተገለጸው።    

ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ በግጭት ምክንያት ከተለያዩ ቦታዎች ከተፈናቀሉ ዜጎች መካከል 1 ሚሊዮን 20 ሺህ የሚሆኑት ወደቀያቸው ቢመለሱም በቂ ምርትና በቂ ገቢ ስሌላቸው ራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ይረዳሉ።  

በአንዳንድ የአገሪቷ አካባቢዎች የመኸር ዝናብ ቀድሞ መውጣት፣ ጎርፍ አደጋ የተከሰተባቸው አካባቢዎች መኖራቸውና በተለይ አርብቶ አደር አካባቢዎች ለተከታታይ ሦስት ዓመታት ድርቅ መከሰቱ የተረጂዎችን ቁጥር ከፍ ማድረጉን አስረድተዋል።  

”በምግብ አቅርቦት ላይ 60 በመቶ መንግሥት ለመሸፈን ጥረት ይደረጋል” ያሉት ኮሚሽነሩ በዚህ ላይ ዜጎች፣ ባለሃብቶችና የክልል መንግሥታትን በማስተባበር ድጋፍ የሚያደርጉበት ሁኔታ እንደሚመቻች አመልክተዋል።   

እንደ አቶ ምትኩ ገለጻ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ቀሪውን ወጪ እንዲሸፍኑ ለማድረግ እየተሰራ ነው።     

መንግሥት ከሚሰጠው ድጋፍ ባሻገር ዓለም አቀፍ ማህበረሰብና ለጋሾች ድጋፍ በመስጠት ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል ኮሚሽነሩ።  

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ድጋፍ ፕሬዝዳንት አስተባባሪ አንያስ ቹማ በበኩላቸው እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2018 ዓለም  አቀፉን ማህበረሰብ በማስተባበር በኢትዮጵያ የሰብአዊና የአደጋ ተጋላጮችን መደጋፍ መቻሉን አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ ከ900 ሺህ በላይ ስደተኞችን ተቀብላ እያስተናገደች መሆኗን የገለጹት አስተበባሪው ”ኢትዮጵያዊያን ለተቸገሩ ወንድምና እህቶቻቸው ቀድመው የሚደርሱ መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም” ብለዋል። 

”እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለጋስነቱን በተግባር ማሳየት አለበት፤ ዛሬ ከመቼውም ጊዜ በላይ ኢትዮጵያ የእናንተን ያልተቋረጠ እገዛ ትፈልጋለች” ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ መንግሥት ላቀረበልን ጥያቄ ፈጣንና ወቅታዊ  ምላሽ እንደምንሰጥ ተስፋ አደርጋለሁ ሲሉም ተደምጠዋል አስተባባሪው። 

በተያዘው ዓመት ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን ተደራሽ ለማድረግ ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ ታውቋል።