የትምህርቱ ማሕበረሰብ የጥራት መስፈርቶች ላይ ሊሰራ ይገባል

65
አዲስ አበባ ግንቦት 22/2010 የትምህርቱ ማሕበረሰብ የጥራት መስፈርቶች ላይ በመስራት በአገሪቱ የሚሰጠውን ትምህርት ደረጃ ከፍ ለማድረግ ሊሰራ እንደሚገባ ተገለጸ። መንግስት በመላው አገሪቱ የትምህርት ጥራት ለማምጣት ላስቀመጣቸው ዕቅዶች ስኬት በመንግስትም ሆነ በግል የሚተዳደሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኃላፊነታቸው ሊወጡ ይገባል ነው የተባለው። በአሁኑ ወቅት ከ44 በላይ የመንግስት፣ 130 ደግሞ በግል ይዞታ የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለአገሪቱ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምራት ሞታ ለኢዜአ እንዳሉት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት  የሚሰለጥነውን የሰው ኃይል ብቁና ክሕሎት የተላበሰ የማድረግ ተግባር ትኩረት ሊቸረው የሚገባ ጉዳይ ነው። ተቋማቱ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚሸከም የሰው ኃይል ለማፍራት እየሰሩ ቢሆንም በሚሰጡት ትምህርት ጥራት ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለማስተካከል ሊሰሩ ይገባል ይላሉ።  ተቋማቱ በአገሪቱ የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋፋት የተዘረጋውን እቅድ በማሳካት በኩል ትልቅ ድርሻ የነበራቸው ሲሆን በቀጣይ የትምህርት ጥራትን ለማምጣት በሚደረገው ጥረት የዜግነት ግዴታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ነው ያመለከቱት። በተለይም የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚፈለገውን መስፈርት ያሟሉና በብቃት አገራቸውን ለመረከብ የሚችሉ ዜጎችን በማፍራት ረገድ ጠንክረው መስራት ይገባቸዋል ብለዋል። በመሆኑም በየደረጃው ያሉ የትምህርት ማሕበረሰብ የጥራት መስፈርቶች ላይ በመስራት በአገሪቱ የሚሰጠውን ትምህርት ደረጃ ከፍ ለማድረግ ሊሰራ እንደሚገባ አመልከተዋል። የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማሕበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ሞላ ፀጋዬ በበኩላቸው የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተለይ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት የሰው ኃይሉን በማልማት ረገድ የማይናቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በተለይም ወደ መንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ገብተው መማር የማይችሉ ዜጎች የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን እንደ አማራጭ ተጠቅመው በመሰልጠን በአገሪቱ የተለያዩ የስራ ዘርፎች ውስጥ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑንም አብራርተዋል።  የትምህርት ጥራትን በአንዴ ማስጠበቅ ይከብዳል የሚሉት ዶክተር ሞላ ለትምህርት ተደራሽነት ትኩረት ሰጥቶ እንደተሰራው ሁሉ ጥራትም ላይ ቢሰራ ትልቅ ለውጥ ይመዘገባል ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም