ለሦስተኛ መላ የትምህርት ቤቶች ስፖርታዊ ውድድር ዝግጅት ተጠናቋል

385

መቀሌ የካቲት 28/2011 በአገር አቀፍ ደረጃ በመቀሌ ከተማ የሚካሄደውን ሦስተኛ መላ የትምህርት ቤቶች ስፖርታዊ ውድድር ለማካሄድ ዝግጅት ተጠናቀቀ፡፡

በቢሮው የህዝባዊ መሰረት ስፖርት እድገት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ ካህሱ ዜናዊ ለኢዜአ እንደገለጹት የመወዳደሪያ ሜዳ፣ የተወዳዳሪዎች መኝታ፣ የምግብና የሕክምና አገልግሎት መስጫና ሌሎች ዝግጅቶች ተጠናቅቀዋል፡፡

ለውድድሩ የተለያዩ 13 ኮሚቴዎች ተዋቅረው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ በትምህርት ቤቶች መካከል በሚካሄደው ስፖርታዊ ውድድር የአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ የሁሉም ክልል ትምህርት ቤቶች ተሳተፊ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከመጋቢት 14 አስከ መጋቢት 29 ቀን 2011 ዓ.ም በመቀሌ ከተማ በሚካሄደው አገር አቀፍ መላ የትምህርት ቤቶች ጨዋታ ከእያንዳንዱ ክልልና ከተማ አስተዳደር ከ450 አስከ 600 ተዋዳዳሪዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

እንደ ወይዘሮ ካህሱ ገለጻ በሦስተኛው አገር አቀፍ መላ የትምህርት ቤቶች ጨዋታ በ20 የስፖርት ዓይነቶች ውድድሮች ይካሄዳሉ፡፡

ውድድር ከሚካሄድባቸው የስፖርት ዓይነቶች መካከል አትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ መረብ ኳስ፣ ቅርጫት ኳስና ጠረጴዛ ቴንስ ይገኙበታል፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ባህታ ወልደሚካኤል በበኩላቸው እንደገለጹት ከየክልሉ የሚመጡ ስፖርተኞች የመኝታ ችግር እንዳይገጥማቸው የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

ክልላቸውን ወክለው የሚወዳደሩ ተማሪዎች በስፖርት ውድድር ወቅት የሚባክንባቸውን የትምህርት ክፍለ ጊዜ ለማካካስ በትፍ ጊዜ ድጋፍ የሚያደርጉላቸው መምህራን መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል፡፡

ተወዳዳሪ ተማሪዎች ከሚመጡበት ክልል ለመማር የሚያግዛቸውን የድጋፍ ደብዳቤ ይዘው እንዲመጡም አመልክተዋል፡፡