"ሲንቄ" በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ የድርሻዬን እወጣለሁ--- አምባሳደር ፈቲያ ሙሐመድ

38

አዳማ  የካቲት 28/2011 በኦሮሞ እናቶች የሚከወነው የ"ሲንቄ" ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት  በዓለም ቅርስነት  እንዲመዘገብ በማስተዋወቅ የድርሻውን እንደምትወጣ የባህልና ቱሪዝም  አምባሳደር ፈቲያ ሙሐመድ ገለጸች።

ፈቲያ ሙሐመድ  የ2018 የቁንጅና ውድድር በማሸነፍ ሚስ ኢትዮጵያ በኋላም የባህልና ቱሪዝም  አምባሳደር ሆና ተመርጣለች፡፡

አምባሳደር ፈቲያ ለኢዜአ እንዳለችው በኦሮሞ እናቶች የሚከናወነው  ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ የሆነው "ሲንቄ"  የፆታ እኩልነት እንዲረጋገጥ በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ  መሰረት የጣለ ሥርዓት ነው።

"ሲንቄ" የዓለም ማህበረሰብ እንዲገነዘብ በማድረግ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፥ የሳይንስ እና የባሕል ተቋም /ዩኔስኮ/ በቅርስነት እንዲመዘገብ  የድርሻዋን ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን  ተናግራለች።

"በኦሮሞ እናቶች የሚከወነው የሲንቄ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት  በሰላም እሴት ግንባታ ውስጥ የሀገራችን እናቶች እያበረከቱ ያሉትን አስተዋጽኦ  ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስረዳትና ሁሉም እንዲማርበት ማስቻል አለብን "ብላለች።

ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን  በአውሮፓ፣ አሜሪካና እስያ  ሀገራት እያስተዋወቀች እንደምትገኝ የጠቀሰችው አምባሳደር ፈቲያ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አኩሪ ባህል የሆነውን የሲንቄ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት ለማስተዋወቅ እንደምትሰራ ገልጻለች።

ከዘመናዊ የዳኝነት ሥርዓት በተሻለ መልኩ እኩልነት የሰፈነበትና የፍትህ አሰጣጥ ያለበት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የምዕራብ አርሲ ዞን ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ባለሙያ ወይዘሮ ሳራ ዱቤ ናቸው።

"በኦሮሞ እናቶች የሚከወነው  የሲንቄ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት ሁሉንም የሚያስማማ ውሳኔ የሚሰጥበት ዘመናትን የተሻገረ በግለሰቦችና በቡድን ደረጃ ፍትህ የሚሰጥበት ነው" ብለዋል።

ባለሙያዋ እንዳሉት ሥርዓቱ በአካባቢው ጎሳ መካከል ግጭትና አለመግባባት ሲፈጠር የሚፈታበትና የተጣለው አካል ከመሰረቱ የሚታረቅበት ነው፡፡

የሲንቄ ባህል ድርሻ ግጭትን ከመፍታት ባለፈ ለትዳር የደረሱ  ልጃገረዶችና ወጣቶችን ለመዳር ጭምር ስርዓት ይከናወንበታል፡፡

የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አድማሱ ዋቅጅራ በበኩላቸው ሴቶች ነፃነታቸውን፣መብትና እኩልነት ከሚያረጋግጡበት አንዱ የሲንቄ ስርዓት መሆኑን ተናግረዋል።

የገዳ ሥርዓት ሴቶች ከወንዶች እኩል መብት የሰጠ ሌላው  ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው ሲንቄ "እናቶች በህዝቦች፣በጎሳዎችና ግለሰቦች መካከል የሚፈጠረውን አለመግባባትና ግጭት ለማንም ሳያዳሉ በእኩልነት የሚዳኙበት ነው "ብለዋል።

ባህላዊ ሥርዓቱ ለሀገራዊ ገፅታ ግንባታ ትርጉም በሚኖረው መልኩ ለዓለም  ማህበረሰብ የማስተዋወቅ ሥራ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትኩረት እየሰሩበት መሆኑን አመልክተዋል።

በቅርቡ የሱዳን ልዑካን ቡድን በአርሲ ዞን ኮፈሌ ወረዳ በኦሮሞ እናቶች የሚከወነውን ባህላዊ የስንቄ ግጭት አፈታት ሥርዓት መጎብኘታቸውንና ስርዓቱ ተቋማዊ አደረጃጀት ኖሮት ለዓለም ለማስተዋወቅ እየሰራ መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መግለጹ  ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም